2017-03-23 10:11:00

ቅዱስነታቸው "ክርስቲያኖች በሠሩት ኅጢያት ሊያፍሩ እና ንስሓ ሊገቡ ይገባቸዋል” ማለታቸው ተገለጸ።


“ንስሓ መግባት ማለት በልብስ ማጠቢያ ማሽን ልብሳችን በፍጥነት እና በፈለግነው ዓይነት እንደ ማጠብ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፣ ንስሓ ፈጣን የሆነ ግብይት የማድረጊያ ሥፍራ አይደለም፣ ንስሓ ከኃጢያታችን አንጽቶን ሐሰት በሆነ ይቅርታ የሚደልለን ሥፍራም አይደለም፣ ክርስቲያኖች በሠሩት ኅጢያት ሊያፍሩ እና ንስሓ ሊገቡ ይገባቸዋል”። ይህንን የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው እለት ማለትም በመጋቢት 13/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ካሰሙት ስብከት የተወሰደ ነው።

የዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቅዱስነታቸው በእለቱ ያሰሙት ስብከት ትኩረቱን በእለቱ በላቲን የሥርዓተ ዓምልኮ አቆጣጠር ከትንቢተ ዳኒኤል 5: 25 ላይ በተወሰደው ምንባብ ዙሪያ ያጠነጠነ እንደ ነበረም የታወቀ ሲሆን ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሰው ልጆች በአምላካቸው ፊት በትህትናና በተሰበረ መንፈስ መቆም እንደ ሚጠበቅባቸው የሚያሳስብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሆነም ለመረዳት ተችሉዋል።

“እነሆ ኃጢአት ኃፍረትን የሚያመጣ ነገር ነው። በአንጻሩም ደግሞ እኛ ራሳችን ያጣነውን ፀጋን መልሰን መጎናጸፍ አንችልም” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእለቱ በተነበበው እና ከማቴዎስ ወንጌል 18: 21-35 ላይ በተወሰደው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ሐዋሪያው ጴጥሮስ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው፣ ሰባት ጊዜ ነውን? በማለት ኢየሱስን ጠይቆት እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው  አውስተዋል።

“ኢየሱስም ሰባት ጊዜ ሳይሆን ‘እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት’ ነው” በማለት መልስ ሰጥቶት እንደ ነበረ በመጥቀስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ይቅር መባል እና ይቅርታ” ምን እንደ ሆነ መረዳት ከቻልን እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት እንድንችል ይረዳናል ብለዋል። “ይህም ዛሬ በተነበበው የወንጌል ክፍል ውስጥ የተጠቀሰው ያበዳሪው ጌታ እና የተበዳሪው አገልጋይን ምሳሌን በምንመለከትበት ወቅት፣ ከላይ የተጠቀሰሱትን ይቅር መባል እና ይቅርታን ማድረግ የሚሉትን ጭብጦች በተግባር መረዳት እንችላለን ያሉት ቅዱስነታቸው ጌታው ለአገልጋዩ የዕዳ ስረዛ በማድረግ ይቅርታን አድርጎለት ነበረ፣ ነገር ግን ይህ አገልጋይ የእርሱ ባልጀራ የሆነውን ሰው ዕዳ ግን መሰረዝ እና ይቅር ማለት አልቻለም፣ ይህንንም ያደረገው ይቅርታ ምን ማለት እንደ ሆነ ባለመረዳቱ የተነሳ ነው” ብለዋል።

ይቅርታ ምን እንደ ሆነ ለመረዳት በይቅርታ ሚስጢር ውስጥ ራሳችንን ማስገባት ሕይወታችን እንድትታደስ ይረዳታል ያሉት ቅዱስነታቸው በዚህም ረገድ የእግዚኣብሔር ድንቅ ተግባር በልባችን ይሰርጻል ብለዋል። የንስሓን ምንነት ጠንቅቀን ማወቅ ያስፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንን ካልተገበርን ግን ከንስሓ ስፍራ ወጥተን ከጓደኞቻችን ጋር በምንገናኝበት ወቅት ሌሎች ሰዎችን ማማት እንጀምራለን ኃጢያት መስራቱንም እንቀጥላለን ብለዋል።

ይህንን ዓይነት ተግባር የምንፈጽም ሰዎች ከሆንን በወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ዕዳው የተሰረዘለት አገልጋይ እርሱ ይቅርታ ቢደረግለትም ነገር ግን ሌሎችን ይቅር ማለት እንዳልፈለገው ዓይነት አገልጋይ እንሆናለን ያሉት ቅዱስነታቸው “ይቅርታን ማድረግ የምንችለው ይቅር መባላችን ሲገባን ብቻ ነው” ካሉ ቡኃላ ይቅር መባል ምን ማለት መሆኑን ሲገባን ብቻ ነው ይቅርታን ማድረግ የምንችለው ብለዋል። የዚህ ዓይነት ባሕሪ ከሌሎች ሰዎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ላይ ተጽኖ ያደርጋል ያሉት ቅዱስነታቸው ይቅር ባይነት ጠቅለል ያለ ይዘት ያለው ነው፣ ነገር ግን ይቅር ማለት የምችለው እኔ የራሴ ኃጢያት እንደ ውርደት ሲሰማኝ ብቻ ነው ብለዋል። በኃጢያት ምክንያት የተዋረድኩኝ መስሎኝ ሲሰማኝና እግዚኣብሔር ይቅር እንዲለኝ ስጠይቀው፣ በእግዚኣብሔር ይቅር እንደ ተባልኩኝ ሲሰማኝ፣ ሌሎችንም ወንድሞች እና እህቶች ይቅር ማለት እችላለው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ካልሆነ ግን ሌሎችን ይቅር ማለት አንችልም ካሉ ቡኃላ በዚህም ምክንያት ይቅርታን ማድረግ ማለት ሚስጢራዊ የሆነ ነገር ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንዳሳሰቡት እኛ ይቅር እንደ ተባልን ሁሉ ሌሎችንም ይቅር ማለት ይገባናል ካሉ ቡኃላ “ዛሬ ይህንን በአግባቡ መረዳት እንችል ዘንድ እንዲረዳን፣ ይህንንም የምንረዳበትን ፀጋ እንዲሰጠን እግዚኣብሔርን ልንለምነው ይገባል ካሉ ቡኋላ በኃጢያታችን እፍረት እንዲሰማንና የቅርታውን መቀበል እንድንችል፣ እንዲሁም ሌሎችን የቅር ማለት እንድንችል ልንማጸነው የገባል ብለው ጌታ ሁሉንም ይቅር የሚል ከሆነ እኔ ማን ነኛና ነው ሌሎችን ይቅር የማልል? በማለት ከጠየቁ ቡኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.