2017-03-07 10:48:00

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው "መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበብ ክፉ ነገሮችን እንድንዋጋ ይረድናል"ማለታቸው ተገለጸ።


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በትላንትናው በየካቲት 26/2009 ዓ.ም. የጠቅላላ አስተምህሮን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ባስደመጡት አስተምህሮዋቸው እንደ ገለጹት የእጅ ስልካችንን አብዝተን እንደ ምንጠቀም ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን በመተማመን አዘውትረን ማንበብ ክፉ ነገሮችን እንድንዋጋ በመርዳት፣ ከእግዚኣብሔር እንዳንርቅ በማድረግ በመልካም ጎዳና ላይ እንድንራመድ ይረዳናል ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

በእለቱ እንደ የላቲን ስርዐተ አምልኮ በመጀመሪያ የዐብይ ጾም ሰንበት በተነበበው እና ከማቴዎስ ወንጌል 4:1-11 በተወሰደው ኢየሱስ ወደ በረሃ ሄዶ በእዚያ ለአርባ ቀን እና ለአርባ ሌሊት በጾመበት ወቅት በሰይጣን እንደ ተፈተነ በሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ መሠረቱን ባደረገ ስብከታቸው እንደ ገለጹት ይህ የዐብይ ጾም ወቅት ወደ ፋሲካ የሚደረግ ጎዞ መሆንን ገልጸው ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ ቡኋላና አስተምህሮውን በይፋ ከመጀመሩ በፊት ወደ በረሃ ሄዶ መጾሙ የኢየሱስን ሕይወት ደረጃ አመላካች ነው ብለዋል።

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ወቅት “ይህ የምወደው ልጄ ነው” የሚል የእግዚኣብሔር ድምጽ ከሰማይ ተሰምቶ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከእዚያም ቡኋላ ነው እንግዲህ ኢየሱስ ተግባሩን በይፋ የጀመረው ተግባሩንም በጀመረበት ወቅት ጠላታችን በሆነው በሰይጣን ፈተና እንደ ነበረም አውስተዋል።

ስይጣን ለሦስት ጊዜያት ያህል ኢየሱስን በበረሃ በመፈተን ክፉ ነገሮችን ድል መምታት የሚያስችለውን  ከታአዝዞ እና ከትህትና መንገድ ኢየሱስን ልያስወጣው ሞክሮ ነበር ያሉት ቅዱስነታቸው  ዘላቂ ባልሆነው በእዚህ ምድራዊ ክብር እና ስኬት እንዲሳብ ገፋፍቶት ነበር ብለዋል።

ከየአቅጣጫው የሚወረወሩትን የሰይጣን የተመረዙ ቀስቶች ኢየሱስን እንደ ጋሻ ሆኖ የተከላከለው በእግዚኣብሔር ቃል ላይ ተመርኩዞ ነበር ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ምንም ዓይነት የግሉን ቃል ሳይጠቀም ፈተናውን የመከተው ከእግዚኣብሔርን ቃል በመጥቀስ እንደ ነበረም ገልጸው በእዚህም ተግባሩ በበረሃ የገጠመውን ታላቅ ፈተና መክቶ በበረሃ ያደረገውን ቆይታ በድል ማጠናቀቁን ጨምረው ገልጸዋል።

በእዚህ በያዝነው በአርባ ቀን የዐብይ ጾም ወቅት ክርስቲያኖች  ኢየሱስ ያሳየንን አብነት በመከተል ከክፉ መንፈስ ጋር የምናደርገውን ውጊያ በእግዚኣብሔር ቃል ላይ ተመርኩዘን መዋጋት ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም የእግዚኣብሔር ቃል የሰይጣንን ፈተና ድል እንድናደርግ ይረዳናል የራሳችን ቃል ግን ከምንም ነገር ሊታደገን አይችልም ብለዋል።

ለእዚህም ነው እንግዲህ መጻፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበብ ይገባናል የምላችሁ በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እና በቃሉ ላይ ማሰላሰል ጠቃሚ ነው ስለ እዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ በመተማመን ማንበብ ይገባል ብለዋል።

አንድ ቀን አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ነበር “የተንቀሳቃሽ ስልካችንን በየጊዜው እንደ ምንጠቀመው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩም መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቀን ብንይዝ እና ብናነብ ምን ሊከሰት ይችል ነበር? ብሎ ጠይቆ እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በተንቀሳቃሽ ስላካችን ላይ ያሉትን መልእክቶች እንደ ምናነብ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የእግዚኣብሔር መልእክት ብናነብ ምን ይከሰት ነበር? በማለት ድግመው ጥያቄን አንስተው በእርግጥ የእግዚኣብሔርን ቃል በየጊዜው ብናነብ ማንኛውም ዓይነት ፈተና ከልባችን ይርቃል በእግዚኣብሔር መንፈስ ተሞልተን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የምንወድበትን ጸጋ መጎናጽፍ እንችል ነበር ብለዋል።

ስለእዚህም የዐብይ ጾም ወቅት መንፈሳዊ ለውጥ በማድረግ ወደ ፋሲካ የሚደረግ ጎዞ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በእዚህም ጎዞ ወቅት የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ በእግዚኣብሔር ቃል፣ በጸሎት፣ በጾም እንዲሁም በመመጽወት  ድል እያደረግን የምንጓዝበት ወቅት መሆኑን ገልጸው ተንቀሳቃሽ ስልካችንን እንደምንጠቀመው ሁሉ በአጠገባችን ያለውን እና በቀላሉ የሚገኘውን የእግዚኣብሔርን ቃል የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳትዘነጉ ካሉ ቡኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተምህሮ አጠናቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.