2017-03-01 14:31:00

"የዐብይ ጾም ወቅት ከኃጢያት ባርነት ወደ ነፃነት የሚደረግ የለውጥ ጎዞ ነው" ሮዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ።


በዛሬው እለት ማለት በየካቲት 22/2009 ዓ.ም. የምሕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዐብይ ጾምን በይፋ የሚጀምሩበት ቀን ነው። ይህም አብይ ጾም በአመድ መቀባት ስነ-ስርዓት በይፋ ተጀምሩዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በዛሬው እለት ማለትም በየካቲት 22/2009 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኝዎች ያስተላለፉት የጠቅላላ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው ከእዚህ በፊት በተከታታይ “የክርስቲያን ተስፋ” በሚል አርዕስት ስያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል ሆኖ፣ ነገር ግን በዛሬ እለት በምሕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት በይፋ የተጀመረውን የዐብይ ጾምን ከግምት ያስገባ አስተምህሮ ማድረጋቸውም ተገልጹዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ዐብይ ጾም የተስፋ ጉዞ ነው በማለት አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው አብይ ጾም የቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮ አንዱ ክፍል እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት ለፋሲካ በዓል ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ገልጸው በእነዚህም 40 ቀናት ውስጥ የፋሲካ ሚስጢር ብርሃንን በመያዝ ወደ ፋሲካ በዓል በተስፋ የሚደረግ ጎዞ ነው ብለዋል።

በፋሲካ የብርሃን ሚስጢር ከሙታን የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ከጨለማ ሕይወት ወጥተን ብርሃን ወደ ሞላበት ሕይወት እንድንገባ ጥሪ ያደርግልናል በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አብይ ጾም ከሙታን ወደ ተነሳው ወደ ክርስቶስ የሚደረግ ጉዞ ነው ብለዋል።

ስለእዚህም የአብይ ጾም ወቅት የሱባዔና ተጋድሎ የምናደርግበት ወቅት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም የምናደርግበት ምክንያት ለእራሳችን ብለን ሳይሆን፣ ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞት አብረን እንነሳለን በሚል እሳቤ ሊሆን ይገባል ካሉ ቡኋላ ይህንንም በምናደርግበት ወቅት ሁሉ በጥምቀት የገባነውን መሀላ በድጋሜ በማደስ  ከላይ በሚመጣው የእግዚኣብሔር ፍቅር በድጋሜ የምንታደስበት፣ የምንነጻበት ወቅት ነው ብለዋል።

ይህንን ጽንሰ ሐሳብ በሚገባ ለመረዳት እንችል ዘንድ በኦሪት ዘጸአት ላይ ተጠቅሶ የሚገኘውን እስሬራኤላዊያን በግብጽ በጭቆና ስር በነበሩበት ወቅት በከፍተኛ ለቅሶ እና ስቃይ ውስጥ ገብተው በነበሩበት ወቅት ምንጊዜም የሕዝቡን ስቃይና ለቅሶ የሚያዳምጥ እግዚኣብሔር በሙሴ አማካይነት በባርነት ቀንበር ሥር ከነበሩበት ከግብጽ እንዲወጡ በማድረግ ለ40 ዓመታት በበረሃ ውስጥ በጠንካራ ክንዱ እየመራቸው ወደ ነጻነት እንደ ወሰዳቸው ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ መልኩም እነዚህ 40 የዐብይ ጾም ቀናት ለእኛ ለክርስቲያኖች ሁላችን ከባርነትና ከኋጢያት ተላቀን  ወደ ነፃነት በመጓዝ ከክርስቶስ ጋር የምንገናኝበት ወቅት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው እያንዳንዱ እርምጃ፣ ድካም፣ ፈተና፣ ውድቀትና ከውድቀት መነሳት፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ትርጉም ሊሰጡን የሚችሉት በእግዚኣብሔር የደኅንነት እቅድ ውስጥ አስቀምጠን ስንመለካታቸው ነው ካሉ ቡኋላ ይህንንም ግምገማ በምናደርግበት ወቅት እግዚኣብሔር የእኛን ሞት ሳይሆን መዳናችንን፣ ስቃያችንን ሳይሆን ደስታችንን እንደ ሚፈልግ መገንዘብ እንችላለን ብለዋል።

ዐብይ ጾም “መንፈሳዊ ለውጥ የምናደርግበት ወቅት ሊሆን ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንን የአብይ ጾም ወቅት ተገቢው በሆነ መልኩ የሚጓዝ ሰው በለውጥ መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ ይገኛል ብለው የዐብይ ጾም ወቅት ከኋጢያት ባርነት ወደ ነፃነት የሚደረግ የለውጥ ጎዞ ነው ብለዋል።

ነገር ግን በረሃን ማቋርጦ መጓዝ ቀላል ነገር አይደለም በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በበርሃ ውስጥ ድካም፣ ፈተና፣ ጥርጣሬ የመሳሰሉት ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ካሉ ቡኋላ ከእነዚህም ነገሮች ውስጥ ልክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ልጁዋ በመከራ ውስጥ በነበረበት ወቅት ሁሉ በታላቅ እምነት ከሙታን እንደ ሚነሳ እና የእግዚኣብሔር ፍቅር ሁሌም አሸናፊ እንደ ሚሆን አምና በተስፋ እየተጠባበቀች እንደ ነበረች ሁሉ እኛም ተስፋ መቁረጥ አይገባንም በእዚህም ተስፋ ተሞልተን የአብይ ጾም ወቅትን በታላቅ ደስታ እና ተስፋ መጀመር ይጠበቅብናል ካሉ ቡኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን አስተምህሮ አጠናቀዋል። 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.