2017-02-23 10:04:00

ጾም ምንድነው? መጾምስ ለምን አስፈለገ? ክፍል ሁለት


ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን ባለፈው እሁድ የካቲት 12/2009 ዓ.ም. የተጀመረውን አብይ ጾምን አስመልክተን ለእናነት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ጾምን በተመለከተ ጠቃሚ ያልናቸውን መረጃዎች እና አስተምህሮዎችን ወደ ማቅረብ ጀምረናል። የእዚህ ዝግጅት ቀጣይ የሆነውን ክፍል ዛሬ ለእናንተ እናቀርብላቹኋለን  እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የእዚህን አስተምህሮ ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!


ክፍል ሁለት

ጾም ምንድነው? መጾምስ ለምን አስፈለገ?

ስለ ጾም አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተዘርዝሮ ከሚገኙ በርካታ አመላካች ከሆኑ ጥቅሶች ውስጥ የተወሰኑትን ማጣቀሻ ይሆናችሁ ዘንድ ለእናንተ እናቀርብላችኋለን።

የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር 1992 ዓ.ም. ባሳተመው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስድስተኛ እትሙ ላይ ጾምን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል።

ጾም በብሉይ ኪዳን ውስጥ

በሐይማኖታዊ ምክንያት ያለ ምግብና ያለ መጠጥ መዋል (መ. አስቴር 4.16)፣ ከሥጋና ከሚያረክስ መጠጥ መታቀብን ያመለክታል ይለናል (ትንቢተ ዳኔል 10. 2.3)። ሙሴ አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ጾመ (ዘዳግም 9:9,19)። የእስራኤል ሕዝብ በማስተሰሪያ ቀን እንዲጾሙ ታዘዙ (ኦ. ዘሌዋዊያን 16. 29-31)። ከባቢሎንም ምርኮ ቡኋላ ለእስራኤል ሕዝቦች አራት የጾም ጊዜያት ታወጁ (ት. ዘካሪያስ 8.19)። ከእነዚህም ሌላ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተነሳ የግል ጾም (2ሳሙኤል 12:22) ወይም ደግሞ የማኅበር ጾም (መ.መሳፍንት 20:26, በተጨማሪም በመጽሐፈ ኢዮብ 1:14) መታወጁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እናገኛለን።

በተጨማሪም ጾም ሐዘንን (መ. ነህምያ 1:4)፣ ንስሓን (1ሳሙኤል 7:6)  ላይ እንደ ተጠቀሰ ያሳያል። ሰዎች በጾም ራሳቸውን አዋረዱ (መዝሙር 69:10)፣ የእግዚኣብሔርን እርዳታ ፈለጉ (ዘጸሃት 34: 28፥ ዕዝራ 8:21-23) የሚለውን ያሰማናል። ነብያትም ጾም ምን ማለት እንደ ሆነ በመልካም ሁኔታ ገልጸዋል (ኢሳያስ 58: 1-12፣ ኤርሚያስ 14:11,12) የተጠቀሱትን በጾማችን ወቅት ምን ማድረግ እንዳለብን እና በጾማችን ወቅት ለባልንጀሮቻችን መልካምን ነገር በማድረግ በእግዚኣብሔር ፊት ሞገስ አግኝተን ለኋጢያታችን ካሳ፣ ለነብሳችን ፈውስ፣ ለስጋችን ደግሞ ጤናና በረከት የምናገኝበት ወቅት እንዲሆን መፈጸም የሚገባንን ተግባራትን ይዘረዝራሉ።

በአዲስ ኪዳን ዘመን ደግሞ ልክ በሐዋሪያት ሥራ 27:9 እንደ ተጠቀሰው አይሁዳዊያን የማስተሰሪያ ጾምን አከበሩ ይለናል። ፈሪሳዊያንም በሳምንት ሁለት ጊዜ ሰኞና ሐሙስ ይጾሙ ነበር (ሉቃስ 18:12) ላይ መንበብ ያቻላል። እነ ሐናም ብዙ ጊዜ ይጾሙ ነበር (ሉቃስ 2:37)፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀን መጾሙንና ለእኛም የጾምን አስፈላጊነት አስተማረ (ማቴዎስ 4:2) ላይ እንደ ተጠቀሰው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር በነበረበት ወቅት አልጾሙም ነበር ወደ አባቱ ከሄደ ቡኋላ ግን እንደ ሌሎቹ እንዲጾሙ ነገራቸው ይለናል የማቴዎስ ወንጌል 9: 14-17።

በጾማችን ወቅት ሁሉ እግዚኣብሔርን እንጂ ሰውን ማየት እንደ ማይገባ መጽሐፍ ቅዱሳችን ያስተምረናል (ማቴ. 6:16-18)። ምዕመናን ወንጌላዊያንን ሲልኩ፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን (ቀሳውስትን) ሲሾሙ ይጾሙ እንደ ነበረ በሐዋሪያት ሥራ 13:2 የተጠቀሰውን የባርናባስና የሳውልን ለልዩ ተልዕኮ መመረጣቸውን ይገልጽልናል። ዋንኛው የጾም ዓላማ ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘት ነውና ሰው ሲጾም ጊዜውን ለጸሎት ሊያውል ይገባዋል በመጽሐፈ ዕዝራ 8:23፣ በማቴዎስ 17:21 እና በሉቃስ 2:37 ላይ እንደ ተጠቀሰው። በአጠቃላይ ጾም ምዕመናን ሁለንተናቸውን ከዓለማዊ ሀሳብና ምኞት መልሰው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲያተኩሩና እንዲጸልዩ ያደርጋቸዋል።  

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ጾም ማለት  የርሃብ አድማ መምታት ማለት ሳይሆን ራሳችንን በመግዛት፣ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔርን እና ወንድሞቻችንንን በመውደድ መንፈሳዊ ጸጋ እንድናገኝ የምንጸልይበት የንስሓ ወቅት ነው። ታዲያ ጾም ለእኛ ለክርስቲያኖች የርሃብ አድማ ማለት አይደለም የሚለውን ትርጉም የሚሰጠን ከሆነ በተለይ ለኛ ለክርስቲያኖች ለየት ያለ ትርጉም ሊሰጠን ይገባል ማለት ነው።

“ጾም የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታዊ እውነታዎችን እንድናውቅና በዚህ መንገድ የእግዚኣብሔር ቃል ሕይወታችንን ዘልቆ በመግባት እኛ የሕይወታችን የጉዞ መንገድ ምን መሆን እንዳለበት በማስረዳት ማን እንደሆንን፣ ከየት እንደመጣን ወዴት እንደ ምንሄድ እንድንገነዘብ በማድረግ የሕይወትን መንገድ ያሳየናል” የቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በኔዴክቶስ 16ኛ ከተናገሩት የተወሰደ።

ክቡራን እና ክቡራት ታዳሚዎቻችን ስትከታተሉት የቆያችሁት ባለፈው እሁድ የካቲት 12/2009 ዓ.ም. የተጀመረውን አብይ ጾምን አስመልክተን ለእናነት አንባቢዎቻችን ጾምን በተመለከተ ይጠቅማል ያለውን መረጃ ወደ እናንተ አድረሰናል። በሚቀጥለው አርብ የዛሬ አስተምህሮ ቀጣይ የሆነውን ክፍል ሦስት አስተምህሮን  ለእናንተ እናቀርባለን እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።








All the contents on this site are copyrighted ©.