2017-02-21 11:11:00

ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2009 ዓ.ም የዐብይ ጾም መግቢያ በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት!


ብፅዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2009 ዓ.ም  የዐብይ ጾም መግቢያ በማስመልከት  ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

የእዚህን መልዕክት ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

 

“እግዚአብሔር ራሱ እንዲጠብቀን በጾምና በጸሎት ተማጸንነው እርሱም ጾሎታችንን ሰማ ”  (ዕዝ 8፡23)።

የተወደዳችሁ መዕመናን !

ከሁሉ አስቀድሜ  እንኳን ለ2009 ዓ.ም  የጌታችን የመዳኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዐብይ ጾም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁኝ፡፡ የሁላችን መምህር አርዓያ የሆነው  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውን ጾም በመከተለል  የምንፈጽመው  ዐብይ ጾም ቤተክርስቲያናችን ዛሬም እንደትናቱ በበረሃ ከከቆየው ኢየሱስ ሚስጥር ጋር ራሳን ታዋህዳለች፡፡

ዐብይ ጾም እኛ ምዕመናን የሥጋ ፈቃዳችንን በመተው የነፍሳችንን ፈቃድ በሙሉ ልባችን በማስገዛት የምንጾመው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ራሳችንን ከዓለማዊ ነገሮች በማራቅ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን የምንፈጽመውና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቀርበን የእርሱን ምህረት ደጅ በመጥናት ጌታ ሆይ ማረን ጌታሆይ ራራልን፣ጌታሆይ፣ይቅር በለን በማለት የእርሱን ምህረት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ነው፡፡

የጾም ጊዜ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱበት የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ስለሆነም በጾም፣በጸሎት፣ በሱባኤ ራሳችንን በመለወጥ ለመንፈሣዊ ሕይወት ዕድገታችን መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን የምናበዛበት ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ቤተሰባዊ ቅርርቦሽ የምናሳድግበት፣የገዛ ፍላጎታችንን በመቆጣጠር ለወንጌል የተልዕኮ ሥራዎች የተገባን ሆነን ስለ ሃጢያታችን የምናዝንበት፣ድሆችን የምናስብበት፣ጊዜና በበለጠም እምናታችንን በማጠናከር ለነፍሳችን ስንቅ የምንይዝበት ልዩ ጊዜ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸውንና እግዚአብሔር ልመናቸውን እንዲሰማና የፈለጉትን እንዲሰጣቸው እኛም ጾማችንን በትክክለኛው መንገድ ጀምረን በመፈጸም የኃጢያት ሥርየታችንን ለማግኘት የበቃን  መሆን ይጠበቅብናል፡፡

በአገራችን በኢትዮጵያ ብዙ የመኪና አደጋዎች እንደሚደርሱ በየጊዜው ከትራፊክ ፖሊስ ጽ/ቤት መስማት የተለመደ ሆኗል ፡፡ የብዙ ወገኖቻችን ሕይወት መቀጠፍና መጎዳቱ እንዲሁም አካል ጉዳተኛ መሆን እጅግ ያሳዝናል፡፡ የብዙ ቤተሰብ ሕይወት ባሳዛኝ ሁኔታ ይናጋል፣ብዙ ንብረትም ይወድማል፡፡በተለይ በዚህ ዐብይ ጾም ወራት አደጋው የሚገታበት መንገድ በማሰብ እንድንጸልይና እንድንጠነቀቅ እንዲሁም የትራፊክ ሕጎችንና ደንቦችን እንድናከብር አደራ እላለሁ፡፡ 

 የተከበራችሁ ምዕመናን!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾምና ጾሎት ታላቅ ኃይል ሠሪ መሆናቸውን ሲያስተምር “ እንዲህ ዐይነቱ  በጸሎትና በጾም ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምንም አይወጣም ማር 9፡29”፡፡ በጸሎት መሳሪያነት በሙሉ ልባችን ተነሣስተን ይህን የበረከት ጾም  ለመላው አለም ሰላም፣ እንዲሁም ስለአገራችን ሰላም፣ ስለራሳችንና ስለመላው ህዝበ ክርስቲያን ደኅንነት፣ ስለህመምተኞች፣ስለችግረኞች፣ በመጸለይ እንድናሳልፈው አደራ በማለት ይህን የበረከት ጾም እግዚአብሔር አባት በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተቀብሎ የምናቀርበውን ጾማችንን  ጸሎታችንን ሱባዔያችንን ተቀብሎ ጸጋውንና በረከቱን ይስጠን፡፡

ዐብይ ጾማችንን በሰላም አስጀምሮ በማስጨረስ ጾማችንን የተባረከ የተቀደሰ ያድርገው፡፡

                        እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካት ፣ይጠብቃትም፡፡

+ካርዲናል ብርሃነየሱስ ደምረው ሱራፌል (ዘማኅበረ ልዑካን ‘ላዛሪስት’)

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን

የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

የምስራቅ አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ዋና ጸሐፊ








All the contents on this site are copyrighted ©.