Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ \ ስብከቶች

ቅዱስነታቸው "ብርታት፣ ጸሎትና ትሕትና ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በዓለም ውስጥ እንድታሰራጭ የረዱዋት ባህሪያት ናቸው" አሉ።

ቅዱስነታቸው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት።

16/02/2017 14:05

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ብርታት፣ ጸሎት እና ትሕትና እነዚህ ሦስቱ ባሕሪያት ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በዓለም ውስጥ እንድታስፋፋ የረዱዋት ታላላቅ ሚስዮናዊያን የተላበሱት መለያ ባሕሪያቸው ነው  ማለታቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩት በትላንትናው እለት ማለትም በየካቲት 7/2009 ዓ.ም. በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ሲሆን በእለቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የስርዓተ ሊጡርጊያ አቆጣጠር የተከበረውን የቅዱሳን ቅርሊዮስ እና መቶድየስ አመታዊ ክብረ በዓል በተከበረበት ወቅት መሆኑም ታውቁዋል።

የእዚህ ዜና ሙሉ ቃል ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

እንደ ቅዱሳን ቅርሊዮስ እና መተድየስ ያሉ የእግዚኣብሔርን ቃል የሚዘሩ እውነተኛ የቃሉ አብሳሪ የሆኑ፣ ሕዝቡን ወደ እግዚኣብሔር ማቅረብ የሚችሉ ሚስዮናዊያን በአሁኑ ወቅት ለቤተክርስቲያን ያስፈልጉዋታል በማለት ስብከታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው የእግዚኣብሔርን ቃል በብቃት ለማብሰር የሚረዱ እና እርሳቸው አንድ ሚስዮናዊ ሊጎናጸፍ ይገባዋል ያሉዋቸውን 3 ባሕሪያት እንዳሉም ገለጸዋል።

ቅዱስነታቸው በእለቱ ያሰሙት ስብከት ዋንኛ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በእለቱ የተከበረው የቅዱሳን ቅርሊዮስ እና መተድየስ አመታዊ ክብረ በዓል ላይ እና በእለቱ በተነበቡት ምንባባት ላይ ተመርኩዘው ጳውሎስ እና ባርናባስ ወንጌልን ለማብሰር ያደረጉትን ጥረት እና እንዲሁም በወንጌል በተጠቀሰው ኢየሱስ 72ቱን ደቀ መዛሙርት ሁለት ሁለት አድርጎ እንደ ላካቸው በሚያወሳው የመጻሐፍ ቅዱስ ቃል ዙሪያ ያጠነጠነ ስብከት ማድረጋቸውንም ለመረድት ተችሉዋል።

ቅዱስነታቸው አንድ የወንጌል አብሳሪ ሚስዮናዊ በቀዳሚነት ሊጎናጸፈው የሚገባው ባሕሪ በግልጽነት ላይ የተመሰረት “ብርታት እና ጥንካሬ” ሊኖረው ይገባል ካሉ ቡኋላ የእግዚኣብሔር ቃል በሐዋሪያው ጳውሎስ በኩል እንደ ምያስተምረን “አጥንትን እና ጅማትን ዘልቆ” ይገባ ዘንድ በግልጽነት እና በብርታት ሊሰበክ ይገባዋል በለዋል።

“መንፈሳዊ ብርታትና የልብ ጥንካሬ የሚመነጩት በኢየሱስ ፍቅር ስንማረክ ብቻ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው የግልጽነት ባሕሪን ተላብሰን በብርታት ወንጌሉን ስናበስር ብቻ ነው እውነተኛ የእግዚኣብሔርን ሕዝብ ልንመሰረት የምንችለው ብለዋል።

ያለ ጸሎት የሚሰበክ የእግዚአብሔር ቃል ልክ አንድ ጉባኤን እንደ ማካሄድ ይቆጠራል እንጂ ወንጌልን በአግባቡ አበሰርኩኝ ለማለት አያስደፍርም በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከማርቆስ ወንጌል የወሰዱትን አንድ የወንጌል አብሳሪ ሊኖረው ይገባል ያሉትን ሁለት ባሕሪያትን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በሉቃስ ወንጌል 10.1-9 ላይ የተጠቀሰውን “እነሆ መከሩ ብዙ ነው፣ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሥራ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት” የሚለውን የኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን ቃል በማስታወስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ከብርታት በመቀጠል አንድ ሚስዮናዊ ሊጎናጸፈው የሚገባው ባሕሪ የጸሎት ባሕሪ ሊሆን እንደ ሚገባውም ጨምረው ገልጸዋል።

“የእግዚኣብሔር ቃል ሁልጊዜም ቢሆን በጸሎት ኋይል ነው ሊሰበክ የሚገባው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ያለ ጸሎት በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ጉባሄ ወይም የሕነጻ ትምህርት ማካሄድ ይቻል ይሆናል። ነገር ግን የእግዚኣብሔር ቃል ከልብ ሊመነጭ የሚችለውና የሰውን ሊቀይር የሚችለው  በጸሎት ኋይል ብቻ ነው ብለዋል። ስለዚህም ቃሉን በምትዘሩበት ወቅት እግዚኣብሔር እንዲረዳችሁ መጸለይ ይገባችኋል ያሉት ቅዱስነታቸው የተዘራው ዘር እንዲያድግና ፍሬያማ ይሆን ዘንድ እግዚኣብሔር በጸጋው እንዲያረሰርሰው የወንጌል አብሳሪዎች ሁሉ የጸሎትን አስፈላጊነት ተረድተው መጸለይ ይገባቸዋል ብለዋል።

በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው እና ምርጥ ሊባል የሚችል እውነተኛ የሆነ የሚስዮናዊ ባሕሪ ሊሆን የሚገባው “የየዋህነት መንፈስን መላበስ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በወንጌል እንደ ተጠቀሰው ጌታ ደቀ መዛሙርቱን “እንደ በግ በተኩላዎች መካከል ልኮዋቸው እንደ ነበረም” አስታውሰዋል።

እውነተኛ ወንጌላዊ ድክመቱን የሚያውቅ እና ራሱን በራሱ መከላከል የማይችል መሆኑን የሚረዳ ሰው ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “እንደ ተኩላዎች ሆናችሁ በተኩላዎች መካከል ብትመላለሱ እግዚኣብሔር ሊረዳችሁ አይችልም” የሚለውን የቅዱስ ክሮዞስቶም አባባልን አስታወሰው በተመሳሳይ መልኩም አንድ ወንጌላዊ ራሱን በጣም ብልህ አድርጎ በመቁጠር ብልህነቴን ተጠቅሜ እነዚህን ሰዎች ወደ እግዚኣብሔር እመልሳለሁ ብሎ የተነሳ ወንጌላዊ ሁሉ መጨረሻው ውድቀት ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በስብከታቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ባሕሪያት ማለትም ብርታት፣ ጸሎት እና ትሕትና የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መገለጫ ባሕሪያት ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል ካሉ ቡኋላ እነዚህም ሦስቱ ባሕሪያት ሚስዮናዊያን የእግዚኣብሔርን ቃል እንዲዘሩ እና ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንድትሰፋፋ ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ ባሕሪያት መሆናቸውን ገልጸው በቀድሞ ጊዜያት ብርታትን የተሞሉ የጸሎት ሰዎች እንደ ነበሩም አስታውሰው ቅዱሳን ቅሪሊዮስና መተድየስ እነዚህን ሦስቱን ባሕሪ ተላብሰን ወንጌልን በዓለም ማሰራጨት እንድንችል ያማልዱን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል ካሉ ቡኋላ ለእለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።     

 

16/02/2017 14:05