2017-02-15 16:57:00

ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ጋላገር በረፓብሊካዊት ቸክ አገር


የቅድስት መንበር የውጭ ግኑኝነት ጉዳይ ዋና ጸሓፊ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ፓውል ሪቻርድ ጋላገር የቸክ ረፓብሊክ አገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉቦሚር ዛኦራለክ ባደረጉላቸው ጥሪ መሠረት እ.ኤ.አ. ከየካቲት 9 ቀን እስከ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በቸክ ረፓብሊክ አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት ማካሄዳቸው ሎሶርቫቶረ ሮማኖ የተሰየመው የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው ኅትመቱ ይጠቁማል።

የቅድስት መንበር የውጭ ግኑኝነት ጉዳይ ዋና ጸሓፊ ብፁዕነታቸው ብፁዕ አቡነ ጋላገር በረፓብሊክ ቸክ በሚገኙት በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ልኡክ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ጁዘፐ ላንዛ ለሐዋርያዊ ልኡክነታቸው ዋና ጸሓፊ የኔታ ሚስላቭ ሆድዚችና የሐዋርያዊ ወኪል ቢሮ ሹም የኔታ ጆሰፍ ሙርፍይ ተሸኝተው ባካሄዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከአገሪቱ የመንግሥት የበላይ አካላትና ባለሥልጣናት፡ ከፖለቲካውና እንዲሁም በአገሪቱ ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ጋር መገናኘታቸው ያስነበበው የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ አክሎ፥ በቅድስት መንበር የረፓብሊካዊት ቸክ ልኡከ መንግሥት ፓቨል ቮሳሊክ በተገኙበት ከውጭ ጉዳይ ሚኒ. ዛኦራለክ በውጭ ጉዳይ ሚኒ. ሕንፃ እ.ኤ.አ. የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ተገናኝተው በባህል በሰብአዊ ትብብር ጉዳይ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ግንኙነት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በቸክ ረፓብሊክ አገር ያላት በተለይ በቅርቡ በሁለቱ አገሮች መካከል በተደረሰው የጋራው ስምምነት መሠረት በግብረ ሠናይ በሕንጸትና በጤና ጥብቃ አገልግሎት የምትሰጠው አስተዋጽኦ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸው ጠቅሶ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ነክ ጉዳዮች በመካከለኛው ምስራቅ ክልል ስላለው ውጥረት፡ የአፍሪቃ ወቅታዊ ሁኔታና ግብረ ሽበራና የስደተኞች ጸአት የተሰኙት ርእሰ ጉዳዮች በማድስደገፍ የሐሳብ ልውውጥ ካካሄዱ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒ. ዛኦራለክ የአገራቸው መንግሥት ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ረፓብሊክ ቸክ ይጎበኙ ዘንድ ይፋዊ ጥሪ ማቅረባቸው አስታወቀ።

ብፁዕ አቡነ ጋላገር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተሰናብተው ከአገሪቱ ከአቢያተ ክርስቲያን ከተለያዩ አቢያተ ክርስቲያን እንዲሁም ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር የግኑኝነት ጉዳይ የውክልና ኃላፊነት ካላቸው ከባህል ጉዳይ ሚኒ.ዳኔል ሄርማን ጋር ተገናኝተው የአገሪቱ መንግሥት ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት የተዋጣለት መሆኑ ሚኒ. ሄርማን በማረጋገጥ የአገራቸው የባህል ሃብት 44 በመቶው በሃይማኖቶች ቅርስና በሃይማኖት ባህል የሚሸፈን መሆኑ ሲያበክሩ ብፁዕ አቡነ ጋላገርም በበኩላቸው ከኮሙኒዝም ስርዓት መውደቅ በኋላ ተወርሰው የነበሩት የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ንብረት የነበሩት ሁሉ ለኵላዊት ቤተ ክርስቲያን በመመለሳቸው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመላ አገሪቱ ተልእኮዋ የመፈጸም ነጻነቷ ዳግም እንዲጠበቅ በመደረጉም ምክንያት አመስግነዋል  ያለው የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ አስከትሎም፥ ብፁዕነታቸው በአገሪቱ ከሚገኘው ቅድስት መንበር ከምሥረታው ጀምራ በአባላነት ለምትታቀፍበት የኤውሮጳ አገሮች የደህንነትና የትብብር ድርጅት ልኡክ ስተፋን ፉኤል በአገሪት የውጭ ጉዳይ ሚኒ. ሕንፃ ተገናኝተው የድርጅቱ ሂደት ርእስ ዙሪያ ሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጣቸው ይጠቁማል።

ብፁዕ አቡነ ጋላገር በዚህ በቸክ ረፓብሊክ ሐዋርያው ጉብኝት ባካሄዱበት ወቅት በአገሪቱ ከምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ውስጥ  ከፕራግ ሊቀ ጳጳስ የአገሪቱ የብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ዱካ፡ ከፕራግ ልሂቅ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሚሎስላቭ ቭልክ፡ ለኦሎሙክ ሰበካ ሊቀ ጳጳስ የአገሪቱ ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ዋና ጸሓፊ ብፁዕ አቡነ ያን ግራውብነር ጋር የተገናኙ ሲሆን በግንኙነቱ ወቅትም የቤተ ክርስቲያንና የቸክ ሪፓብሊክ መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት በአገሪቱ የቤተ ክርስቲያን ሚና በአገሪቱ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያዊ ግብረ ኖልዎ ዘርፍ የሚያጋጥማት ተግዳሮቶችና ስደተኞች የማስተናገዱ ጉዳይ መጪው የኤውሮጳ እቅድና በመካከለኛው ምስራቅ ያለው የክርስትያኖች ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢነት በተሰኙት ርእሶች የተወያዩ ሲሆን፡ የብፅዕነታቸው የቸክ ረፓብሊክ ጉብኝታቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው በየጋራ ጥቅም ላይ የጸናው የጋራው ግንኙነትና ትብብር አመርቂነቱ ያረጋገጠ መሆኑ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ በየካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ኅትመቱ አስነብቧል።








All the contents on this site are copyrighted ©.