2017-01-28 10:32:00

ቅዱስነታቸው በክርስቲያኖች መካከል እርቅ ሊመጣ የሚችለው እኛ አንዳችን ለአንዳችን የተሰጠን ስጦታ መሆናችንን ስንቀበል ነው አሉ


ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በክርስቲያኖች መካከል እውነተኛ የሆነ እርቅ ሊመጣ የሚችለው እኛ ክርስቲያኖች አንዳችን ለአንዳችን የተሰጠን ስጦታ መሆናችንን ስንቀበልና አንዳችን ከአንዳችን በትህትና መማር ስንችል ብቻ ነው ማለታቸው ተገለጸ።

የእዚህን ዜና ሙሉ ቃል ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቅዱስነታቸው ይህንን መልእክታቸውን ያስተላለፉት ከጥር 10-17/2009 ዓ.ም. ለአንድ ሳምንት ያህል ለክርስቲያኖች ኅብረት ሲካሄድ የነበረው ጸሎት የማብቂያ ስነስርዓት ላይ ለተገኙ ከተለያዩ እህት አብያተ ክርስቲያናት የተውጣጡ ተወካዮች በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ በተገኙበት ቅዱስነታቸው በመሩት የመዝጊያ ጸሎት ቡኋላ ባስተላለፉት መልእክት መሆኑም ተዘግቡዋል።

ቅዱስነታቸው በእለቱ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የስርዓተ ሉጥርጊያ አቆጣጠር በጥር 25/2017 ዓ.ም. በተከበረው ዕብራዊ የነበረው ሳውል የጌታን ደቀ መዝሙር ለመግደል ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በመንገድ ላይ ተገልጦለት ከክሪስቲያኖች አሳዳጅነት ወደ ታላቅ የክርስቶስ ሐዋሪያነት የተቀየረበት ቀን ከሚታወስበት እለት ጋር መሳ ለመሳ የተከበረውን ለክርስቲያኖች ሕብረት ይደረግ የነበረው የአንድ ሳምንት ጸሎት ማብቂያን አስመልክተው ካሳረጉት የምሽት ጸሎት በማስከተል ያስተላለፉት መልእክታቸው ዋንኛ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው “የክርስቶስ ፍቅር እርቅን እንድንፈጥር ግድ ይለናል” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ያጠነጠነ እንደ ነበረም ለማወቅ ተችሉዋል።

“እርቅ ከክርስቶስ የሚሰጥ ስጦታ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “አማኞች ማንኛውንም ልዩነቶቻቸውን ለማስወገድ ከመጣራቸው በፊት የእግዚኣብሔር ነፃ ስጦታ የሆነውን እርቅን በቅድሚያ መፈጸም ይገባቸዋል” ብለዋል።

“ከምዕተ አመታት በፊት በተፈጠረው ልዩነት ቡኋላ በዛሬው እለት እንዴት ነው የእርቅን የምስራች ቃል መስበክ የምንችለው?” ብለው ጥያቄን በማንሳት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በበኩሉ እርቅን ለመፍጠር መስዋዕትነትን መክፈልና ሥር-ነቀል የሆነ የሕይወት ለውጥ ማድረግ እንደ ሚገባ አውስቶ እንደ ነበረም ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ኢየሱስ እንደ ኢየሱስነቱ ሕይወቱን ለእኛ መስዋዕት አድርጎልናል እኛም የተጠራነው ለራሳችንና ለፍላጎቶቻችን ብቻ እንድንኖር ሳይሆን ሕይወታችንን ለሌሎች መስዋዕት በማድረግ ለክርስቶስና በክርስቶስ እንድንኖር ነው የተጠራነው ብለዋል።

ክርስቲያኖች  ወቅታዊ ከሆኑ ፕሮግራሞች እና እቅዶች፣ በተጨማሪም በፋሽኖች ሳይሆን መጠመድ የሚገባቸው ነገር ግን ትኩረታችንን የሕይወታችን እቅዶችና ፕሮግራሞች ምንጭ በሆነው በክርስቶስ መስቀል ላይ ማድረግ ይገባል በልዋል። ይህም የክርስቶስ መስቀል ልዩነቶቻችንንና ራሳችንን በራሳችን ዘግተን በመኖር መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ውጭ የሚያከናውነውን ምርጥና ድንቅ ተግባር እንዳንቃወም ጥሪ ያቀርብልናል።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት ምንም እንኳን ወደ ሁኋላ መመልከትና ያለፉ ትውስታዎቻችንን ማሰላሰል በጣም ጠቃሚ ነገር ቢሆንም ባለፉት ጊዜያት በተሠሩት ስህተቶች ትውስታ ላይ ብቻ ማትኮር ሰንካላ ያደርገናል፣ በተጨማሪም ዛሬን በአግባቡ እንዳንኖር ያደርገናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተለይም ይህ ንግግራቸው ትኩረቱን ያደረገውና በማጣቀሻነት ሊጠቅሱት የፈለጉት ጉዳይ የካቶሊክና የሉቴራን አብያተ ክርስቲያናት በአሁኑ ወቅት በመዘከር ላይ የሚገኙትን በይፋ የተለያዩበትን 500ኛውን አመት በዋቢነት ለመጥቀስ ፈልገው መሆኑ የታወቀ ሲሆን በእዚህ ወቅት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በቀጣይነት እያደርጉት የሚገኘው ውይይት ከፍተኛ እምርታን እያስገኘ መምጣቱንም አጋጣሚውን ተጠቅመው ገልጸዋል።

ክቡራንና ኩቡራት አድማጮቻችን ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በእርሳቸው መሪነት በእለቱ ከተካሄደው የምሽት ጸሎት ቡኋላ ያስደመጡትንና እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የስርዓተ ሉጥርጊያ አቆጣጠር በጥር 25/2017 ዓ.ም. በተከበረው ዕብራዊ የነበረው ሳውል የጌታን ደቀ መዝሙር ለመግደል ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በመንገድ ላይ ተገልጦለት ከክሪስቲያኖች አሳዳጅነት ወደ ታላቅ የክርስቶስ ሐዋሪያነት የተቀየረበት ቀን በሚታወስበት እለት ጭብጥ ዙሪያ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል እንድትከታተሉን እንጋብዛለን።

ቅዱስ ሐዋሪያው ጳሎስ ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ በነበረበት ወቅት በመንገድ ላይ ከኢየሱስ ጋር መገናኘቱ ሕይወቱን ቀይሮታል። ከእዚያም ቡኋላ የእርሱ ሕይወት በራሱ ክህሎት ላይ ብቻ በመተማመንና በጣም ጥብቅ በሆነ ሕግ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ እና መልካም ፍቅርን የሙጥኝ በመያዝ መስዋዕት ለሆነው እና ከሙታን ለተነሳው ለኢየሱስ ክብር ብቻ በመኖር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱን ሕይወቱን የጀመረው ሕይወቱን በመንፈስ ቅዱስ በመዋጀት ነው።  ከሙታን በተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ምሕረት፣ መተማመን እና መጽናናት ምን ማለት እንደሆኑ ለመረዳት ችሎ ነበር። ሐዋሪያው ጳውሎስ ይህንን ታድሶ ለራሱ ብቻ ሊጠቀምበት አልፈለገም። በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት እግዚኣብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ መስዋዕት አድርጎ የሚያቀርበውን የፍቅር እና የእርቅ መልካም ዜናን መመስከር ጀመረ።

ከእዚህ ቀደም የአህዛብ ሐዋሪያ የነበረ አሁን ደግሞ ከእግዚኣብሔር ጋር ከታረቀ ቡኋላ ግን (2 ቆሮንጦስ 5,20) የክርስቶስ አምባሳደር ሆነ፣ ይህም ከክርስቶስ የተሰጠው ነፃ ስጦታ ነው። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ማለትም ሐዋሪያው ጳሎስ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች የጻፈው 2ኛው መልእክቱ በእዚህ አመት ለተከበረው የአንድ ሳምንት ስለ ክርስቲያኖች ኅብረት ለሚደረገው ጸሎት መሪ ቃል እንዲሆን የተመረጠውም ሀረግ “እርቅን እንድንፈጽም የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል” (2 ቆሮንጦስ 5,14-20) የሚለው የተመረጠው በእዚሁ ምክንያት ነው። “የክርስቶስ ፍቅር” የሚለው ሀረግ እኛ ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ክርስቶስ ለእኛ ያለው ፍቅር ነው እንጂ። በተመሳሳይ መልኩም እየፈጸምነው የምንገኘው እርቅ በራሳችን አነሳሽነት የሚፈጠር እርቅ እንዳልሆነም ማወቅ ይገባናል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ እርቅ እግዚኣብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመካይነት ለእኛ የሚያቀርብልን ስጦታ ነው። እያንዳንዱ አማኝ ሰው በተናጠል ልዩነቶቻችንን ለማሰውገድ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የእግዚኣብሔርም ነፃ የሆነ ስጦታም ታክሎበታል። በእዚህ ነፃ የእግዚኣብሔር ስጦታ አማካይነት እያንዳንዱ ሰው ኋጢያቱ ተሰሪዮለታል እንዲወደድም አድርጎታል በምላሹም የእርቅን መልካም ዜና በቃል እና በተግባር በመኖር እና በመመስከር በእርቅ የተሞላ ሕይወት እንዲኖር ተጠርቱዋል።

ዛሬ በእዚህ ብርሃን ተሞልተን “እንዴት ነው ይህንን የእርቅ ወንጌል ከምዕተ አመታት ክፍፍል ቡኋል መመስከር የምችለው?” ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ ራሱ ይህንን ጥያቄ የመፍቻ መንገድን ያሳየናል። በክርስቶስ አማካይነት እርቅን መፍጠር መስዋዕትነትን እንደ ሚጥይቅ ቅዱስ ሐዋሪያው ጳውሎስ በግልጽ ያስተምረናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም ሰዎች ሕይወትን የሰጠው ለሁሉም በመሞት ነው። በተመሳሳይ መልኩም የእርቅ አባሳደሮች የሆኑት ሁሉ ነብሳቸውን በመስዋዕትነት በማቅረብ፣ ከአሁን ቡኋላ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ሊኖሩት የሚገባው ነገር ግን ለእነርሱ ብሎ ለሞተላቸው እና ከሙተን ለተነሳው ለክርስቶስ እንዲኖሩ በስሙ ተጠርተዋል (2 ቆሮንጦስ 5,14-20)። ኢየሱስ ራሱ  በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ 9,24 ላይ እንደ ሚያስተምረን “ ስለ እኔ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል” ማለቱ ይታወሳል። ይህም ሓዋሪያው ጳውሎስን የገጠመው አብዮት ነው፣ ይህም ዛሬ እና በመጭው ጊዜያት ሁሉ ይህ መርህ የክርቲያኖች አብዮት ሆኖ ሊቀጥል ያስፈልጋል። ከአሁን ጀምሮ ለራሳችን ብቻ ስይሆን መኖር የሚገባን፣ ለራሳችን ፍላጎቶችና ግጽታ ብቻ ሳይሆን መኖር የሚገባን ነገር ግን ለክርስቶስ ገጽታ ግንባታ ለእርሱ እና ለእርሱ ብቻ በመኖርና እርሱን በፍቅር በመከተልና በእርሱ ፍቅር በመኖር ሊሆን ይገባል።

ከእርሱ እና እርስ በእርሳችን እርቅን ማስፈን እንድንችል ይረዳን ዘንድ እግዚኣብሔር የእርቅን ስጦታ ይሰጠን ዘንድ በምንጠይቅበት ወቅት እዚህ የተገኛችሁትን የተለያዩ እህት ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች የሆናችሁትን ሁሉ ይህንን ጥሪ አክብራችሁ እና አስፈላጊነቱንም በጥልቀት ተረድታችሁ እዚህ በመገኘታችሁ ማስጋናዬ የላቀ ነው። በተለይም ደግሞ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በምሳራቃዊ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል   እየተደረገ ባለው የሥነ-መለኮታዊ የውይይት ኮሚሽን አባላት እዚህ በመገኘታችሁ በጣም ደስተኛ መሆኔን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ። በቀጣይነትም ይህ በሥነ-መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ የጀመራችሁት ምምክርና ውይይት ፍሬያማ ይሆን ዘንድ እመኛለሁኝ።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ለክርስቲያን ሕብረት የምናደርገው ጸሎት ምንጩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱ “አባት ሆይ! እኔ የምለምንህ ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ነው” (የሐንስ 17,21) ብሎ ከመጸለዩ ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን ስጦታ እግዚኣብሔር የሰጠን ዘንድ ከመጸለይ መታከት የለብንም። በታላቅ ትዕግስ እና እግዚኣብሔር አባታችን ሁሉንም ክርስቲያኖች አንድ እንደ ሚያደርጋቸው ተስፋ በማድረግ በእዚህ አሳብ ሕይወታችንን ወደ ፊት መግፋት ይኖርብናል የእርቅ እና የወይይት ጎዳናን መያዝ ይኖርብናል፣ ለክርስቶስ ስም ብለው ራሳቸውን በጀግንነት መስዋዕት ያደረጉትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን፣ ያለፉትን ይሁን አሁን የሚገኙትን ሁሉ ማስታወስ ይገባናል። አብረን በጋራ የመጸለይ አጋጣሚዎች በተገኙበት ወቅቶች ሁሉ የእግዚኣብሔር መለኮታዊ ጥበቃ እንዳይለየን በመጸለይ በጋር እርሱን እንድንመሰክር፣ በጣም ድኸ የሆኑትን እና አስታዋሽ የሌላቸውን ሰዎች ሁሉ በጋራ እንድንወድ እና እንድናገለግል እርሱ ይርዳን። አሜን!

ክቡራንና ኩቡራት አድማጮቻችን ስትከታተሉት የነበራችሁት ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የስርዓተ ሉጥርጊያ አቆጣጠር በጥር 25/2017 ዓ.ም. በተከበረው ዕብራዊ የነበረው ሳውል የጌታን ደቀ መዝሙር ለመግደል ወደ ደማስቆ በመሄድ ላይ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በመንገድ ላይ ተገልጾለት ከክሪስቲያኖች አሳዳጅነት ወደ ታላቅ የክርስቶስ ሐዋሪያነት የተቀየረበት ቀን በሚታወስበት እለትን ምክንያት በማድረግ እና ከጥር 10- 17/2009 ዓ.ም. ለክርስቲያን ሕብረት በተደረገው ጸሎት ማብቂያ ላይ በእርሳቸው መሪነት በተካሄደው የምሽት ጸሎት ቡኋላ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ለተገኙ የተለያዩ ሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ያሰሙትን ስብከት ነበር ዝግጅታችንን በትዕግስ ስልተከታተላችሁ ከልብ እናመሰግናል።

 

 








All the contents on this site are copyrighted ©.