2017-01-26 11:29:00

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ "ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ብርታት አላቸው" ማለታቸው ተገለጸ።


ቅዱስነታቸው ልማዳዊ በሆነው መልኩ ዘወትር ርዕቡና እሁድ እለት የጠቅላላ አስተምህሮ እንደ ሚያስተላልፉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬ እለት ማለትም በጥር 17/2009 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ምዕመናንና የሀገር ጎብኝዎች በተገኙበት ያስተላለፉት ጠቅላላ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው ከእዚህ በፊት የክርስቲያን ተስፋ በሚል አርዕስ ያደረጉት አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

የእዚህን ዜና ሙሉ ይዘት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!

ቅዱነታቸው አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በብሉይ ኪዳን ውስጥ በአብነት ከተጠቀሱት ሴቶች መካከል በሕዝቡ እንደ ታላቅ ጀግና ተደርጋ የምትቆጠረውን የዮዲትን ታሪክ ያቀርብልናል” በማለት አስተምህሮዋቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሚገኘው የመጽሐፈ ዮዲት ውስጥ እንደ ተጠቀሰው የቤቱላ ከተማ የሶሪያ የጦር ጄነራል በነበረው በሆሎፈርነስ በተከበበችበት ወቅት በእዚያ የነበሩ ሕዝቦች በሁኔታው ተደናግጠው እጅ ለመስጠት በቋፍ ለይ እንደ ነበሩ መጽሐፈ ዮዲት እንደ ሚያወሳ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

በሁኔታው የተደናገጡና ተስፍ የቆረጡ የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በአምላክ በመተማመን፣ ጌታ ጣልቃ ገብቶ እንደ ሚታደጋቸው በመተማመን ለአምስት ቀናት ያህል እጅ ላለመስጠት ወስነው እንደ ነበረ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው ሕዝቡ በእዚህ መከራ ውስጥ በነበረበት ወቅት በድንገት ከተፍ ያለችው ዮዲት ወራሪውን የጠላት ኋይል ማሸነፍ የሚቻልበትን እቅድ ይዛ በመቅረቡዋ ሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ ብርታት ሊሰማው እንደ በቃም ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የእዚህች በጥበብ፣ በማስተዋልና በታላቅ ብርታት የተሞላች ሴት ምሳሌ በእግዚኣብሔር መልኮታዊ ጥበቃ ማመን አስፈላጊ መሆኑን  ያስተምረናል በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ጸሎት የመጸለይና የታዛዢነት መንፈስን በማዳበር ለእርሱ ፈቃድ ራሳችንን ተገዢ በማድረግ በሕይወት ጎዳናችን ላይ የሚገጥሙንን ማንኛውንም ዓይነት ፈተናዎች ኋያላችንን አሙዋጠን በመጠቀም ማሸነፍ እንደ ሚቻልም ገልጸዋል።

የዮዲት እምነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ጌተሰማኒ እንዲሄድ የገፋፋውን የእግዚኣብሔርን ፈቃድ የመፈጸም አስፈላጊነትን እድንረዳ ያነሳሳናል ያሉት ቅዱስነታቸው በምንጸልይባቸው ወቅቶች ሁሉ “የኔ ፈቃድ ይሁን” ብለን መጸለይ ሳይሆን የሚጠበቅብን ነገር ግን “ያንተ ፈቃድ ይሁን” ብለን ወደ እግዚኣብሔር መጸለይ እንደ ሚገባም በአጽኖት ገልጸዋል።

የተስፋ ጉዞ ማለት በሕይወታችን የሚገጥሙንን መሰናክሎች በኋላፊነት በመወጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ወደ ፊት መራመድ ማለት ነው በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም የተስፋ ጉዞ በምናጓዝበት ወቅቶች ሁሉ ራሳችንን ለጌታ ፈቃድ በማስገዛት ሊሆን እንደ ሚገባም አስምረውበታል።

የህም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ዮዲት ጥበባዊ እቅዱዋን ከመተግበሯ በፊት በጣም ብዙ በመጸለይ ተከታታይ የሆነ ውይይቶችን ከሕዝቡ ጋር ካደረገች ቡኋላ ከእዚያም በታላቅ ብርታት ወደ ጠላቶቹዋ የጦር አዛዢ በመቅረብ አንገቱን የቆረጠችሁ በእምነቷ ላይ በነበራት ታላቅ እምነት እና ይህንም እምነቷን በተግባር በማሳየቷ ምክንያት እንደ ነበረም ቅዱስንታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

“ይችህ በብርታትና በእምነት የተሞላች ሴት በሞት ሽረት ውስጥ የነበሩ ሕዝቦቹዋን ወደ ተስፋ መንገድ እንዲመለሱ አድርጋ ነበር፣ ይህም ለእኛ ታላቅ ተምሳሌት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው በሕይወታችን “እከሌ እኮ ጥበበኛ ነው፣ እከሊት እኮ ከፍተኛ ብርታትና ትሕትና ያላት ሰው ናት” የሚሉትን አባባሎችን ብዙ ጊዜ የሰማችሁ የመስለኛል ካሉ ቡኋላ ነገር ግን ጠለቅ ብለን በምናስብበት ወቅት እነዚህ ሰዎች ይህንን ክህሎት ያገኙት ከእግዚኣብሔር መሆኑን እንረዳለን ብለዋል። ብዙን ጊዜ ሴቶች ትክክለኛ ቃላትን መጠቀምና የተስፋ ቃላትን የመለገስ ችሎታቸው ከፍተኛ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህንንም ችሎታ የተጎናጸፉት ከፍተኛ የሆነ የሕይወት ተሞክሮ ስላላቸውና በሕይወታቸው ከፍተኛ የሆነ መከራ ሰለሚገጥማቸው ችግሮቻቸውን ሁሉ ለጌታ በአደራ ስለሚሰጡና እርሱም ይህን ችግር መወጣት የሚችሉበትን ጥበብ ሰለ ሚለግሳቸውና ተስፋን ስለሚሰጣቸው እንደ ሆነም ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው ማጠቃለያ ላይ እንደ ገለጹት በሕይወታችን ዘመን ሁሉ “አባት ሆይ! ፍቃድህ ቢሆን ይህንን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፣ ግን ያንተ ፈቃድ እንጂ የእኔ ፋቅድ አይሁን!” ብሎ ኢየሱስ እንደጸለየ ሁሉ ይህንን የጥበብ፣ የመተማመንና የተስፋ ተምሳሌት የሆነውን ጸሎት እኛም አዘውትረን መጸለይ ይገባናል ካሉ ቡኋላ አስተምህሮዋቸውን አጠናቀዋል።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.