2016-10-17 14:01:00

አባ ሮበርቶ በርጋማስኪ ለሐዋሳ ሀገር ስብከት አዲስ ጳጳስ ተሾመ።


ታላቅ እንደ ታናሽ መሪ እንደ አገልጋይ ይሁን

የብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ቃለ ምዕዳን

መስከረመ 28 ቀን 2009 ዓ. ም. ሀዋሳ

 

ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ሊዊጂ ቢያንካ

ብፁዕን ጳጳሳት

ካህናት፣ ደናግላን፣ ወንድሞች

 ካቲኪስቶች፣ ምዕመናን

ጥሪያችንን አክብራችሁ የተገናችሁ በሀዋሳ ከተማ የምትገኙ  ሃይማኖት አባቶችና የመንግስት ተጠሪዎች

ዛሬ ክቡራን ወንድሞቼና እህቶቼ እዚህ የተሰበሰብነው የወንድማችንን የአባ ሮበርቶ በርጋማስኪ ሲመተ ጵጵስና ለማክበርና ከእርሳቸው ጋር ሆነን እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለመለመን ነው፡፡ ስለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ለልዑል ለቅዱስ እግዚአብሔር  ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡ እነሆ አሁን ወንድማችን አባ ሮበርቶ ሊቀበሉት የተዘጋጁትን ከፍ ያለ የቤተክርስቲያናዊ ሃላፊነት  በጥንቃቄ እንመልከት፡፡

 

የሰውን ልጅ ለማዳን ከአብ የተላከው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በተራው 12 ሐዋርያት  ወደ ዓለም ላከ  እነኝህ ሰዎች ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ እና እያንዳንዱን  ዘርና ሕዝብ  በቅድስና መንገድ የሚተዳዳር አንድ መንጋ ለመሆን ያበቁት ዘንድ  በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ተሞሉ ፡፡ ይህ አገልግሎታቸው እስከ ዛሬ ዘመን ፍፀሜ ድረስ ቀጣይ  በመሆኑ ሐዋርያቱም እንዲሁም ሌሎች  ረዳቶች መረጡ ሐዋርያቱ ከክርስቶስ የተቀበሉትን  የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምስጢረ ክህነት  በምላት በማስተላለፍ  በአምብሮተ እድ  ለረዳቶቻችው ያስተላልፋሉ፡፡  በዚህ ዓይነት መንገድ  ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ሳይቋረጥ  በመጣው የጳጳሳት መተካካት በመጀመሪያ የተሰጡት ስልጣናት ሲተላለፉ የቆዩት ሲሆን የአዳኙ ሥራ እንዲሁ ህያው ሆኖ  በእኛም ዘመን ሲያድግ ይታያል፡፡ ለዘላለም ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በካህናቱ  መካከል በቆመው ጳጳስ አምሳል እነሆ አሁን ከመካከላችሁ ይገኛል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ለሐዋርያቶቹ እንዲሁ  ለተከታዮቹ በሰጠው ቃል መሰረት  አንድና ወይም ሁለት ሰዎች  በፀሎት አብረው ሲፀልዩ   በመካካላችሁ  እገኛለሁ  ባለው መሰረት እኛ ዛሬ የህብረት ፀሎት ስናደርግ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ እናምናለን፡፡ 

በጳጳሱ  አገልግሎት አማካይነት ክርስቶስ ራሱ ወንጌልን የማወጅ  ተግባሩና  ለአማኞች  የሃይማኖታቸውን  ምስጢር  ማስተማሩን ይቀጥላል፡፡ በጳጳሱ አባታዊ  ተግባር ክርስቶስ አዳዲስ አባላትን በአካሉ ይጨምራል፡፡ የጳጳሱን ጥበብ አስተዋይነት በመገልገል ክርስቶስ ወደ ዘላለማዊ  ደስታ በምታደርጉት ምድራዊ ጉዞ ይመራችኃል፡፡

ስለዚህ እነሆ እጀን በመጫን የማህበረ ጳጳሳት አባል አድርገን ልንቀበለው የተዘጋጀነውን  ወንድማችን አባ ሮበርቶ  በደስታና በምስጋና ተቀበሉት፡፡

የክርስቶስ አገልጋይና የአምላክ ምስጢራት ጠባቂ በመሆኑም አክብሩት፡፡  የወንጌልን እውነት የመመስከርና  የፍትህና የቅድስና መንፈስ  የማስፈን ታላቅ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ጌታ እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል  እናንተን ያልተቀበለ እኔን አልተቀበልም  እኔን ያልተቀበሉት ደግሞ የላከኝን አልተቀበሉም ባለው መሰረት ለሐዋርያቱ የተናገረው ቃል  አስታውሱ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ምዕመናን ክቡር ወንድማችን  አባ ሮበርቶን  ማክበር እንዲሁም ስለ እርሳቸው  መፀለይ ያስፈልጋል፡፡ በጥዋትና ማታ ፀሎት፣ በመቁጠሪያ ፀሎት፣ በተለይ  በመስዋዕተ ቅዳሴ   ስለ አባታችን አቡነ ሮበርቶ ብለን መፀለይ እንጀምራለን፡፡

ምክንያቱም የክርስቲያን ሀይሉ ፀሎቱ ነው፡፡ እርሳቸው ይሄን የተሰጣቸው ሃላፊነት መውጣት የሚችሉት  እኛ ከጎናቸው በመሆን ለእርሳቸው በመፀለይና  በሳቸው  ለመመራት ስንችል ነው፡፡

ውድ ወንድሜ አባ ሮበርቶ ሆይ አንተ በጌታ ተመርጠሀል ከሰዎች   መሀል እንደተመረጥህ ከአምላክም ጋር  ሆነህ ስለ ወንዶችና ሴቶች  እንድትሰራ መሾምህን  አስታውስ፡፡ ጵጵስና የክብር ሳይሆን የአገልግሎት ማዕረግ ነው ፡፡ ስለዚህ ጳጳሱ ከማስተዳደር ይልቅ አገልግሎት ለመስጠት መጣር አለበት፡፡ የጌታን ምክር ያዘለ ቃል እንዲህ ስለሚል  እናሳታውሰው፡፡ ታላቅ እንደ ታናሽ፣ መሪም እንደ አገልጋይ ይሁን፡፡ ተቀባይ አገኘም አላገኘም መልዕክቱን  አውጅ  በታላቅ ትህትና  ትምህርት ስህተትን አርም፡፡ በነፍስ እረኝነት ስር ለሚገኘው ሕዝብ ፀልይለት፡፡ መስዋዕት አቅርብለት፡፡ ይህን በማድረግም ተርፎ ከሚፈሰው የክርስቶስ ቅድስና  መላው ሕዝብ ማንኛውንም አይነት ፀጋ እንዲገኝ ትጋ፡፡ ታላቅ መሆን የሚሻ  እንደ ታናሽ ይሁን፣ መሪም እንደ አገልጋይ ይሁን ይላል የጌታ ምክር፡፡ ጌታ ራሱ ወንጌልን በሚያስተምርበት ጊዜ ያሳየው ተግባር እርሱ ሐዋርያቱ  አንተ መምህር ነህ አንተ ጌታ ነህ  ብለው በሚቀበሉበት ጊዜ እርሱ ራሱን  ዝቅ አድርጎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ  ታላቅ ቢሆንምታናሽ መሆኑን ያሳየበት ትምህርት ነው፡፡

በቤተክርስቲያናችን የመሪ ሥራ አገልግሎት ነው፡፡ መሪ አገልጋይ ነው፡፡ይሄንንም ነው ለሌሎች ማስተማር የሚጠበቅብን ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ  ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ  የተናገረው መልዕክት አለ፡፡ ተቀባይ አገኘም አላገኘም  መልዕክቱን አውጀ ወይም ቢመችም ባይመችም ወንጌሉን አውጀ፡፡ ቢቀበሉህም ወይም ባይቀበሉህም  ኃጢያተኖችን ገስጽ ፣ስህተትን አርም፣ የነፍስ እረኛ ነህና  ለሕዝብ ፀልይ፡፡

እንግዲህ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ ሶስት የተለያዩ ተግባራት አሉት፡፡

የመጀመሪያው ማስተማር ነው፡፡ ጌታ ባዘዘው መሰረት  ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና ለሰው ሁሉ ወንጌልን አስተምሩ ባለው መሰረት ጳጳስ የእምነት አስተማሪ ፣ የእውነት መሪ ፣ የወንጌል አብሳሪ ነው ፡፡  ይሄ ነው ትልቁ ሥራ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕዝብ ማገልገል ነው፡፡ የፀጋ አገልጋይ  ካህን ነው፡፡ የምስጢራት  አዳይ ነው፡፡ ምስጢራት ለምዕመናን እንደሚያስፈልጉ የታወቀ ነው  እነዚህ ምስጢራትን ጳጳሱ ማደል የሚችሉት  ደግሞ ከካህናቱ፣ ከደናግል፣ ከካቴኪስቱ፣ከወንድሞች ጋር በመሆን ነው፡፡ ህዝብን ወደ እግዚአብሔር መሳብ የእግዚአብሔርን ፀጋ  የሚያገኙበት ምስጢራትን ማደላደል መቻል ሁለተኛ ተግባሩ ነው፡፡

ሶስተኛው ተግባሩ እኔ ለእናንተ   እንዳደረኩት እናንተም  እንዲሁ ለሌላው እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ  ብሎ ጌታ  በዩሐንስ ወንጌል እንደተናገረው ጳጳስ የሕዝብ  እረኛ፣  አገልጋይ፣ አሰተዳዳሪ ነው፡፡ ሹመት ሳይሆን አገልግሎት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ  ተግባሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡

ሁላችንም በትልቅ አክብሮት የምናስታውሳቸው በዚህ ሰበካ ያለፉት ጳጳሳት የተወጡት ይሄን ሃላፊነት ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጋስፓሪኒ ሆኑ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ  ሕይወታቸውን ለዚህ ሰበካ  አሳልፈው ሰጥተው  አልፈዋል፡፡መልካም እረኛ ነፍሱን ለሌሎች ያኖራል፡፡

ዛሬ ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ  አባ ሮበርቶ ለዚህ አገልግሎት እግዚአብሔር መርጧቸዋል፡፡ እርሳቸው እዚህ ሀገረስብከት መቼም ጳጳስ ሆኜ አገለግላለሁ ብለው  ፈልገው  የመጡ ሳይሆን  እግዚአብሔር  ለኤርምያስ  በመጀመሪያው መልዕክቱ እንደተናገረው አይዞህ አትፍራ ሂድ እኔ ወደምልክህ  ቦታ ሂድ  እዚያም ሄደህ ሕዝቡን ታገለግላለህ  ባላቸው መሰረት ነው ወደዚህ የመጡት ፡፡ አትፍራ እኔ ካንተጋር ነኝ እንዳለው እግዚአብሔር ለኤርሚያስ በዚህ መንፈስ ነው እርሳቸውም የመጡት፡፡

ስለዚህ አባ ሮበርቶ ብቻቸውን ሳይሆን  ከካህናት፣ ከገዳማወያን፣ ከካቲኪስቶች፣ ከወንድሞች፣ ከምዕመናን ጋር ሆነው እንዲሁም ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ህብርት ጋር ሆነው፣  በአጠቃላይ በዚህ ሀገረስብከት  ካለው ሕዝብና ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን  ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ነውና  ይህንን አገልግሎት  የሚቀበሉት በታላቅ ትህትና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ነውና  እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡

 

ኢትዮጵያ ሀገራችን ደስ የምትል አገር ናት፡፡ የብዙ ብሔር አገር መሆንዋን ፣የታላቅ ታሪክ ባለቤት አገር መሆንዋን  ይህም ሕዝብ ተከባብሮ ተደጋግፎ  የመሰረታት ሀገር መሆንዋን  ለመግለጽም ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን አንድ ሆነን  በዘር  በጎሳ  ሳንለያይ  በአንድ ላይ  እግዚአብሔርን  ስናመልክ  በአንድ ላይ ሀገራችንን ስንገነባ ነው እንጂ ስንለያይ አይደለም፡፡ ስንለያይማ  የሚታየውን ነገር አይተናል፡፡ እርስ በእርስ መጠላላት ብቻ ሳይሆን  መገዳደልም አለ፡፡  በስንት ልፋት የተገነባውን ማፍረስ አለ፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ  እንደልብ መጓጓዝን  የሚገታበት  ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ልክ ዛሬ እንደተፈጠረው ማለት ነው፡፡

ብዙ ጳጳሳት ከሀገርም ውስጥ ሆነ ከውጪ አገር  ወደዚህ ለመምጣት አስበው ያልቻሉ አሉ ብዙዎች  ምዕመናን ከዚህ ሀገረስብከት ወደዚህ መጥተው  አብረው ለመፀለይ ለማመስገን  አስበው ነበር ግን አልቻሉም  ከመንገድ የተመለሱም አሉ፡፡

ለዚህች አገር ነው ዛሬ በተለይ መፀለይ የሚገባን፡፡  የእግዚኦታ፣ የሐዘን ጊዜ ነው በአገራችን፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን እንዲያምርባት  ሁልጊዜ  የሚጠብቃት የእግዚአብሔር ፀጋ፣ የኢትዮጵያ አምላክ አሁንም እንዲጠብቃት ነው  አብረን ዛሬ በተለይ መፀለይ የሚገባን፡፡  ደግሞ ይህቺ አገር በተለይ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተሰጠች ሀገር ናት፡፡  ይህ ካቴድራል  የኪዳነምህረት  የእናታችን ካቴድራል ነው፡፡ በእመቤታችን  አማላጅነት  የኢትዮጵያን  ሕዝብ  ለቅሶ፣ ጩኸት፣ ጭንቀት  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  ወደ ልጅዋ መድኃኔዓለም  አቅርባ ሰላም እንድታሰጠን የምንፀልይበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ቋንቋ እግዚአብሔርን በደስታ ለማገልገል የምንችለው የእግዚአብሔር ፀጋ  ከእኛ ጋር ሆኖ ከመካከላችን ክፍውን ሲያስወግድልን ነው፡፡  ዲያቢሎስ ሰይጣን የማይወደው  ነገር ፍቅርን ነው፣ አንድነትን፣ ሰላምን ነው፡፡ ይህ እንዲናጋና እርስ በርሳችን እንድንጠላላ፣  እንድንፋጅ የሚያደርግ ሃይል የሰይጣን  ሃይል ነው፡፡ 

ለዚህ ነው በጥምቀት ጊዜ ካህን ሲጠይቀን  የዳቢሎስን ሥራ ትክዳለህን ብሎ የሚጠይቀው  ትናት እንደካድነው ዛሬም በእግዚአብሔር ጸጋ  አዎ እክዳለሁ  የምንለው ለዚሁ ነው፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ  ከዚህ ሁሉ ከክፉ ሁሉ ጠብቆ አገራችንን ሰላም ያድርግልን ፡፡

እንደምታውቁት ዘንድሮ ብፁዕ ወቅዱስ ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ያወጁት የምህረት ዓመት ነው፡፡ በዚህ የምህረት ዓመት  እርስ በራሳችን  ይቅር እንድንባባል  #የሰማዩ አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ ;/ሉቃ 6፡36/ ባለው መሰረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምህረቱን በሀገራችን  እንዲያወርድ እንፀልያለን፡፡  እርሱ ነው ዘላቂ ምህረት ሊሰጥ የሚችለው፡፡ ዘላቂ ሰላም መስጠት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላም ለማግኘት አብረን እንፀልያለን፡፡ አቡነ ሮቤርቶ ይህንን ጵጵስና ሲቀበሉ ብቻቸውን አይደለም

በዚህ ሀገረ ስብከት አገልግለው ያለፉትን ሁሉ ጳጳሳትን፣ ካህናት፣ ደናግላንን ወንድሞች፣ ካቴኪሰቶች፣ ምዕመናንን ሁሉ፣ በፀሎት ከእርሳቸው ጋር ናቸው፡፡

ቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ፣ ቅዱስ ዶን ቦስኮ፣  ቅድስት ቴሬዛ ዘካከልኩታ የሰበካው ባልደረቦች  ከእነሱ ጋር ሆነን እግዚአብሔርን እናመስግን፣ አማላጅነታቸውን አጥብቀን  እንለምን

ኢትዮጵያ ሰላም እንድታገኝ  ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር ሆነን እንፀልይ፡፡   








All the contents on this site are copyrighted ©.