Social:

RSS:

የቫቲካን ሬድዮ

ከዓለም ጋር የሚወያይ የር.ሊ.ጳጳሳትና የቤተ ክርስትያን ድምጽ

ቋንቋ:

ቤተ ክርስትያን \ ኢትዮጵያ

የሰንበት ዘመስቀል ቃለ እግዚኣብሔር በክቡር አባ መብራቱ ኋ/ጊዮርጊስ።

ሰንበት ዘመስቀል - RV

04/10/2016 15:30

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ

ሳምንቱን በሙሉ ስንወጣና ስንወርድ፣ እራሳችንን እና ቤተሰቦችንን በሚገባ ማስተዳደር ያስችለን ዘንድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወንን ቆይተን እነሆ ዛሬ ደግሞ ልክ በመጽሐፍ ቅዱሳችን እንደተገለጸው “እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ባሕርንና በውስጡም ያሉትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን አርፎአልና ስለዚህም እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው ቀደሰውም” (ዘፀአት 20.11) እኛም ይህን የሰንበት ቀን እንድናከብረው እና እንድንዘክረው፣ ለተደረገልን መልካም ነገር ሁሉ እንድናመሰግንው፣ ለፈጸምናቸው በደሎች ሁሉ ይቅርታን እንድንጠይቀው፣ ስለራሳችን፣ ስለቤተሰቦቻችን ስለሀገራችን እና ለዓለማችን ሰላም እና ብልጽግና የምንጸልይበት ቀን በመሆኑ የሰንበት ቀንን ልዩ ያደርገዋል።

ነገር ግን  እዚህ የተገኘነው ሁላችን የእግዚኣብሔር ልጆች በመሆናችን የተነሳ በቤቱ የመገኘት መብት ያለን ብሆንም ቅሉ፣ ሁላችንም የተገባን እና ንጹሐን ነን ማለት ግን አይቻልም። በኋጥያት የወደቅንባቸው ጊዜያት ይበዛሉ፣ ወንድም እና እህቶቻችንን ያስቀየምንበት ጊዜያቶችም በሕይወታችን ይከሰታሉ፣ እራሳችንንና ጠፈጥሮንም ቢሆን የበደልናባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። በአጠቃላይ ምንም እንኳን ተገቢዎች ባንሆንም በምሕረቱ የሚደግፈን እና የሚጠበቅን እግዚኣብሔር ከምሕረቱ የተነሳ ወደ ፊቱ ቀርበን ማርኝ በምንልበት ወቅት ሁሉ እርሱ ለምሕረት የፈጠነ ልቁጣ ግን የዘገዬ በመሆኑ ምሕረትን ያጎናጽፈናል።

የዛሬ ሰንበት “ሰንበት ዘመስቀል” ይባላል።

ይህ ሰንበት ይህንን ስያሜውን ያገኘው ባለፈው ማክሰኞ ማለትም በመስከረም 17 ከተከበረው የመስቀል በዓል ቡኋላ ያለ ሰንበት በመሆኑ ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማዳን መስዋዕትነትን የከፈለበትን ቀን ለመዘከር እና በተጨማሪም በመስቀሉ የተዋጀን እኛ ክርስቲያኖች የመሰቀሉን ክብር እና አዳኝነቱንም ጭምር እንድንመሰክር መጠራታችንን ለማስታወስ ነው።

የዛሬው የመጀመሪያ ምንባብ የተወሰደው 1 ቆሮንጦስ 1.10-31 ሲሆን የሚገልጸውም በቆሮንጦስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተከሰተው መለያየት ነው።  ሐዋሪያ ጳውሉስ የቆሮንጦስን ክርስቲያናች ልዩነትን በመፍጠራቸው የተነሳ “ወንድሞቼ ሆይ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ እርስ በእርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለው” ይላል።

ሐዋሪያው ጳውሎስ “ወንድሞቼ ሆይ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት ዋንኛው ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ ሁሉ በመስቀሉ የተዋጁ በመሆናቸው የተነሳ የአንዱ የክርስቶስ ቤተሰብ አካል ሆነዋል እና እንደ የአንድ ቤተሰብ አባል እንደ ሆኑ ወንድሞች በመሆናቸው የተነሳ ነው። በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚያምኑ ሁሉ ልዩነታቸውን አስወግደው አንድ የሚያደርጋቸውን የክርስትና ሕልውናን ሊላበሱ ያስፈልጋል።

ዛሬ በምንኖርባት ዓለም ሐይማኖት ትክክለኛ እሴቱን እንዲያጣ እያደረገ የሚገኘው ዋንኛው ነገር ይህ በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠረው ልዩነት ነው። ሁሉ ሰው ክርስቲያኑም ይሁን ያልሆነም ጭምር በሁሉም ነገር ላይ ተስማምተው አንድ አቋም ይኑራቸው ማለት አይቻላም። የሰው ልጆች እንደ የባሕል ወጋቸው፣ እንደ ትምህርት ደረጃቸው፣ እንደ የሀገራቸው ሁኔታ . . .በእነዚ የተለያዩ ተጨባጭ ሁኔታዎች የተነሳ የተለያየ አቋም ሊኖራቸው ይችላል። ሁሉም በአንድነት በአንድ ነገር ላይ መስማማት ቢችሉ እስየው ነበር። ነገር ግን ይህንን ማረጋገጥ ግን የማይቻል ጉዳይ ነው።

ነገር ግን ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁላችን ልናረጋግጠው የምንችለው አንድ ትልቅ እውነታ አለ። በጋራ አንድ አቁዋም ላይ ለመድረስ የምያስችለን አንድ ነገር አለ። በአንድነት መመስከር የምንችለው አንድ አካል አለ። ይህም የሰላም አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን በማስከተልም ክርስቶስ ያስተማረን እና መስዋዕትነትን የከፈለበት፣ እንዲሁም እኛ ክርስቲያኖች እንድናከብረው እንድንከተለው፣ እንድንተገብረው አደራ ያለን ነገር ቢኖር እግዚኣብሔር አባታህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ሕይወትህ በፍጹም ኋይልህ ውደድ የሚለው ቀዳሚው ሲሆን ተከታዩ ደግሞ ባልንጀሮቻችንን እንደ እራሳችን አድርገን መውደድ እንዳለብን የሚያሳየው ነው። በሁለቱም ትዕዛዛት መካከል አንድ የተጠቀሰ የጋራ የሆነ ቃል አለ፣ ይሄውም ፍቅር የሚለው ነው።

ስለዚህም ክርስቲያኖች እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን እና አንድነታቸውን ለመጠበቅ በእነዚህ ሁሉት ትዕዛዛት ላይ የተመሰረተ የፍቅር ምስክርነትን ሊሰጡ ይገባል ማለት ነው። በአጭሩ ክርስቲያኖችን አንድ የሚያደርጋቸው፣ የጋራ አቁዋማቸው፣ የአንድነት መገለጫቸው ፍቅር ነው ማለት ይቻላል። ፍቅር የማይለግስ እና የማይቀበል ሰው ክርስቲያን ነው ማለት አይቻለም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ።

ሐዋሪያው ጳውሎስን  በዛሬ መልዕክቱም የሚለን ይሄኑን እውነታ ነው የሚያረጋግጠው “አንዱ የጳውሎስ ነኝ ሲል፣ ሌላው የአጵሎስ ነኝ ሲል፣ ሌላው ደግሞ የኬፋ ነኝ፣ ሌላው ደግሞ የክርስቶስ ነኝ” ይሉ በነበረበት ወቅት ጳውሎስ በንዴት “ክርስቶስ ተከፍሎዋልን? ብሎ ጥያቄን ያቀርባል።

ለመሆኑ እነዚ ሰዎች እናማን ናቸው? ብለን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።

ጳውሎስ እራሱ በቆሮንጦስ ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት የነበረው ሰው ነው። ኬፋ የሐዋሪያ ጴጥሮስ ሌላኛው ስሙ ሲሆን በቆሮንጦስ ጴጥሮስን የተከተሉት ከአይሁድ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች በቆሮንጦስ እንደ ነበሩም ይገመታል። ስለዚህም ክርስቲያኖች በሰው ጥበብ ላይ ተመስርተው ሳይሆን እምነታቸውን ማጠነከር የሚጠበቅባቸው ነገር ግን አንዱን ክርስቶስን ብቻ በመመልከት የክርስትና እምነት ዋነኛው እሴት የሆነውን ፍቅርን ማጠናከር እና ማንም ይሰብክ ማንም የአንድነታቸው መሰረት ክርስቶስ መሆን ይገባዋል።

የዛሬው ሁለታኛው ምንባብ የተወሰደው ከ1ጴጥሮስ መልዕክት 4.1-11 ሲሆን ጽንሰ ሐሳቡም ለእግዚኣብሔር መኖር አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጽ እና ለእግዚኣብሔር የማይገቡትን ነገር ግን አሕዛብ የሚፈጽሙትን “መዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት መኖርን፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለልክ በመጠጣት፣ በአጸያፊ የጥሆት አምልኮት የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን የብቃ” ይለናል።

ከእነዚህ ነገሮች ክርስቲያኖች ይላቀቁ ዘንድ መንቃት ይጠበቅባቸዋል በተጨማሪም በእግዚኣብሔር መንፈስ በመታገዝ ከእንደነዚህ ዓይነት ድርጊቶች በቆጠብ እና በአንጻሩም የእግዚኣብሔርን ፀጋ መጎናጸፍ የሚያስችለንን ፍቅር በመላበስ ከእነዚህ እግዚኣብሔር ከማይፈልጋቸው ተግባራት እራሳችንን ማላቀቅ ይጠበቅብናል። “ፍቅር ብዙ ኋጥያትን ያሸንፋል እና ከሁላም በላይ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ “ ይለናል ሐዋሪያው ጴጥሮስ። ፍቅር በደልን ይቅር ይላል፣ ፍቅር መቀራረብን ያመጣል፣ ፍቅር በሰላም እንድንኖር ያደርጋል፣ ፍቅር መተሳስብን ያመጣል፣ ፍቅር አንድነትን ያጎናጽፋል፣ ፍቅር የማያጎናጽፈው መልካምነት የለም፣ የእዚህ አይነቱን ፍቅር ነው ክርስቶስ ይሰተማረን እና እንድንኖረው አደራ የሚለን። ክርስቲያኖችን ከሌሎች የሚለያቸው ዋንኛው ነገር ይህ ነው ፍቅር።

የዛሬው ወንጌል በመጀመሪያ ሲነበብ እንደ ሰማነው የተወስደው ከማርቆስ ወንጌል 8.27-38 ድረስ ያለው እና ጴትሮስ ስለ ኢየሱስ ያለውን ግንዛቤ የገለጸበት ነው። ኢየሱስ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል”? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን በጠየቀ ጊዜ የተለዩ መልሶች ነበር የተሰጡት።

“መጥምቁ ዩሐንስ ነው ይሉኋል” የተባለበት ምክንያት ኢየሱስ ልክ መጥምቁ ዩሐንስ እንዳደረገው ሰዎችን ወደ ንስሐ ይጠራቸው ስለነበር፣ እንዲሁም መጥምቁ ዩሐንስ እንዳደረገው በበረሃ በጾም እና በጸሎት ለአርባ ቅናት መቆየቱ ከዩሐንስ ጋር ስላመሳሰለው ነው።

“ኤሊያስ ነህ ይሉኋል” ያሉበት ምክንያት ደግሞ ነቢዩ ኤሊያስ  በእግዚኣብሔር ኋይል ከሙታን ሰዎችን አስነስቱዋል፣ የተራበን በበረከት አጥግቡዋል. . . ይህም ባህሪው ከኢየሱስ ጋር ስለተመሳሰላባቸው ነው ኤሊያስ ነህ ይሉኋል ያሉት።

ዛሬ ለእኔና ለእናንተ ኢየሱስ ማን ነው? ተመሳስይ ጥያቄን ኢየሱስ ለእኔ እና ለእናንተ ብያቀርብልን እና “እኔን ማን ትለኛለህ? ወይም ትይኛለሽ?” ቢለን ምን ዓይነት መልስ እንሰጠዋለን? ምን አልባትም ከጴጥሮስ ኮርጀን አንተ ክርስቶስ ነህ! ልንል እንችል ይሆናል። ብለንም ከሆን ክርስቶስ ለእኔና ለአንተ፣ ለእኔና ለአንቺ ዛሬ ምንድነው? ምን ፋይዳ አለው? በሕይወታችን፣ በኑሮዋችን፣ በሀገራችን . . .ወዘተ. . .

ኢየሱስ በመጀመሪያ ለሐዋሪያቶቹ ያቀረበው ጥያቄ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” የሚለው ነበር። “ሰዎች” ማለቱ ከሐዋሪያት ወገን ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን ማለቱ ነው። መጥምቁ ዩሐንስ፣ ኤሊያስ፣ ከነብያት አንዱ፣ ብለው ነበር የመለሱት ሌሎች ሲሉ የሰሙትን ማለት ነው፣ በሰፈር በምንደር፣ በከባቢያቸው በሚመላለሱበት ቦታ ሁሉ በጥያቄው መሰረት ስለእርሱ የሰሙትን ነበር የነገሩት እንጂ የራሳቸው አመልካከት አልንበረም።

ዛሬም እኛ የአንዱ የአዳኛችን የክርስቶስ ስም በተለያዩ ሁኔታዎች ሲጠቀሱ እንሰማለን። አንድ አንዴም ክርስቶስ አዳኛችን የማይመጥነው ስም ሲሰጠው እናያለን። አዳኝነቱ፣ መሐሪነቱ፣ አባትነቱ፣ እረ ስንቱ ተነግሮ ይቻላል ሁሉ ይረሳና በየመንገዱ ላይ የሚያጋጥሙን አንድ አንድ ክርስቲያን ነን ባዮች የክርስቶስ እውነተኛ ገጽታ በመቀየር ክርስቶስን በማስፈራሪያነት ስፈርጁትም እናያለን።ለምሳሌም በእርሱ ካላመንን ወደ ገኋነብ እሳት እንደሚወረውረን፣ ትዕዛዝቱን በምንጥስበት ወቅት ከሰማይ እሳት አውርዶ እንደ ሚያቃጥለን፣ ኋጥያትን ስንፈጽም እንደ ሚያጠፋን አድርገው ያቀርቡታል። እውነት ነው ስህተቶችን ስንፈጽም ፣ ኋጥያት ስንሠራ፣ ሰውን ስንበድል . . .ወዘተ ክርስቶስ ዝም ብሎ ይመለከተናል ማለት ግን አይደለም። የክርስቶስ ትልቁ ገጽታ መረሳት የለበትም ነው እያልኩኝ ያለሁት። አባት ነው፣ መሐሪ ነው፣ አፋቃሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፣ እንደሰው ለፍርድ አይቸኩልም፣ ይታገሳል ወደ እርሱ እስክንመለስ ድረስ በትዕግስት ይጠባበቃል፣ መሐሪ አባት ስለሆነ።

ክርስቶስን መስብክ ከተፈለገ መሐሪነቱ አፋቃሪነቱ እና ደግነቱ በቀዳሚነት ሊሰበክ ያስፈልጋል እንጂ የማስፈራሪያ ቃላትን መጠቀም ተገቢ አይደለም።

ኢየሱስ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ካለ ቡኋላ እና ሰዎች ስለሱ ያላቸውን አመለካከት ከተረዳ ቡኋላ. . . ያስከተለው ጥያቄ “እናንተስ እኔን ማን ትላላችሁ?” የሚለው ነበር። ዛሬ ክርስቶስ ለእኔ እና ለእናንተ ማነው? ክርስቶስ ለአንተ፣ ክርስቶስ ለአንቺ ማን ነው? ይህንን ጥያቄ ዛሬ በየግላችን መልስ ልናበጅበት ያስፈልጋል። የእያንዳንዳችን መልስ ግን ይለያያል፣ መለያየትም ይገባዋል ምክንያቱ ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ጸጋ እንደ አስፈላጊነቱ ስለሆነ።

ነገር ግን መትወቅ የሚገባው ዋናው ነገር ሁላችንም ለክርስቶስ የምንሰጠው አንድ የጋራ ስም አለ። ይሄውም መሐሪ፣ አፋቅሪ፣ ታጋሽ የሚሉ ቅላት ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ነው እኛ ክርስቲያኖችን አንድ የሚያደርጉን እሴቶች እነዚህ ናቸው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

ክርስቶስ ማን መሆኑን በይበልጥ እንድንረዳ እና በሕይወታችን እርሱን መኖር እንችል ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ከልጇ እንድታማልደን ልንጸልይ ያስፈልጋል።

የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን። አሜን!!

 

04/10/2016 15:30