2016-08-16 12:21:00

“ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጓዋት የቢሮ ሰራተኞች ሳይሆኑ የመንፈስ ቅዱስ እሳት በልባቸው የሚንቦለቦል ሚሲዮናዊያን ናቸው”


ቅዱስ አባታችን ፍራንቸስኮ በነሐሴ 8-2008 ለጠቅላላ አስተምህሮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ያስተላለፉት መልዕክት ትኩረቱን አድርጎ የነበረው “የመንፈስ ቅዱስ እሳት” በሚል አርዕስት ዙሪያ ሲሆን በመልዕክታቸውም “ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጓዋት ቢሮክራትስ ወይም የቢሮ ሰራተኞች ሳይሆኑ የመንፈስ ቅዱስ እሳት በልባቸው የሚንቦለቦል ሚሲዮናዊያን ናቸው” ማለታቸው ተገለጸ።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸውን እንዳስጠነቀቁት ያለዚህ ማለትም ያለመንፈስ ቅዱስ እሳት ቤተ ክርስቲያን እና መላው የክርስቲያን ማህበረሰቦቹዋ  የመቀዝቀዝ ወይም ለብ የማለት አደጋ እንደ ሚያጋጥማቸው ገልጸው ይህንን መልዕክት የሚያዳምጡ ሁሉ እራሳቸውን ይመረምሩ ዘንድ አጋጣሚውን ተጠቅመው ጥሪ ማድረጋቸው ታውቁዋል።

በዕለቱ ከተነበበው እና ከሉቃስ ወንጌል ከምዕራፍ 12:49-53 በተወሰደው የወንጌል ቃል ላይ ተመርኩዘው እና “እኔ የመጣሁት በምድር ላይ እሳት ለመለኮስ ነው። አሁኑኑ ቢቀጣጠል ምንኛ ደስ ባለኝ!” በሚለው በኢየሱስ ቃል ላይ ተንተርሰው ቅዱስነታቸው እንደገለጹት ኢየሱስ “መንፈስ ቅዱስ ልባችንን እንዲያበራው እና አፍቃሪዎች እንድንሆን ይፈልጋል” ብለው “ይህ የመንፈስ ቅዱስ እሳት የማንጻት እና የማደስ ኋይል” ያለው መሆኑን በአጽኖት ገልጸው የሰው ልጆችን መከራ፣ እራስ ወዳድነትን፣ ኋጥያትን ሁሉ በማስወገድ ውስጣችንን አድሶ ዳግም እንድንወለድ ያደርገናል በማለት ገልጸዋል።

በመቀጠልም ቅዱስነታቸው እንዳብራሩት “ እራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ለመንፈስ ቅዱስ ተግባራት ክፍት በምናደርግበት ወቅት፣ በአንጻሩ መንፈስ ቅዱስ ብርታቱን እና ኢየሱስን ለማውጅ የሚያስችለንን ጣዕም በመፍጠር አጽናኝ የሆነውን የምሕረት ምልዕክት ለሁሉም ማዳረስ የሚያስችለንን ብራታ ያጎናጽፈናል” ብለው “ነገር ግን ይህ የመንፈስ ቅዱስ እሳት የሚጀምረው ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ መሆን እንዳለበት” አመልክተዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን ከማንኛውም ፍርሀት ተላቃ በዓለም ውስጥ በሚገባ ለማከናወን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልጋታል” በማለት አስተምህሮዋቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ፍርሃት እና ስሌትን ከግምት በማስገባት ሰላማዊ ወይም ምቹ በሆኑ ቦታዎች ውስጥ ቢቻ መንቀሳቀስ እንደ ማይገባ” ገልጸው እነዚህ ሁለት ባህሪያት ቤተ ክርስቲያንን “አስተዳደራዊ መዋቅርን ብቻ መሰረት ያደርገች ወይም ችግሮችን እና ስጋቶችን የማትጋፈጥ ብሮክራቲክ ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን ያደርጋታል” ብለዋል።

“ነገር ግን መሆን ያለበት እውነታ” አሉ ቅዱስነታቸው “መንፈስ ቅዱስ እሳቱን በልባችን ውስጥ እንድያጡዋጡፍ እና እንቅፋቶችን እና ግድግዳዎችን የመገርሰስ ሐዋሪያዊ ብርታቱን አጎናጽፎን መፍትሄ ፈጣሪዎች በመሆን ቃሉ ያልተዳረሰባቸውን አከባቢዎች እና ምቹ ያልሆኑ መንገዶችን መጓዝ እንድንችል እንዲሁም ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት ሁሉ ይረዳን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ልንጋብዘው ያስፈልጋል” በማለት በአጽኖት ገልጸዋል።

“ከመቸውም ጊዜ በላይ ርኅራኄን የተሞሉ እና መልካም ባልንጀራ በመሆን ወደ ሁሉም በተለይም በመከራ ላይ ለሚገኙ፣ ወደ ተቸገሩ፣ በተለያዩ ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ወደ ሚገኙ እና ወደ ተቸገሩ በተለይም ወደ ስደተኞች መድረስ የሚችሉ ካህናት፣ ገዳማዊያን እንዲሁም ምዕመናን ያስፈልጋሉ” ብለዋል።

መልካም ምሳሌን በማሳየት በታላቅ ፍቅር እና ታማኝነት ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ወንጌልን በዓለም ውስጥ  እያበሰሩ የሚገኙትን ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ምዕመናንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው እንደገለጹት “ የእነዚህ ሰዎች መልካም ምሳሌነት የምያስታውሰን ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጓት ብሮክራት እና ትጉ የቢሮ ሰራተኛ ሳይሆኑ ሕዝቦችን ሁሉ አጽናኝ ወደ ሆነው የክርስቶስ ቃል የሚመልሱ ቅንሃት ያላቸው ሚስዮናዊያንን ናቸው” በማለት በአጽኖት ገልጸዋል።

“ይህንን የመንፈስ ቅዱስ እሳት ቤተ ክርስቲያን ካልተቀበለች እና ወደ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ካልፈቀደች ቤተ ክርስቲያን ቀዝቃዛ ወይ ለብ ያላች በመሆን ሕይወት መስጠት የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርሳለች” ያሉት ቅዱስነታቸው “ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ እሳት ስለሌላት በቀዝቃዛ ወይ ለብ ባሉ ክርስቲያኖች የተገነባች በመሆኑዋ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በአስተምህሮዋቸው ማገባደጃ ላይ እንደ ገለጹት እናታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በአማላጅነቷ የቀዘቀዘውን ልባችንን በመንፈስ ቅዱስ እሳት ታሞቀው ዘንድ እንድትረዳን ልንማጸናት ይገባል ብለው  ቅዱስ ማክስሚላን ኮልቤ እንደ ምያስተምረን “እግዚአብሔርን እና ባልንጄራን መውደድ የሚያስችለንን የፍቅር እሳት ይሰጠን ዘንድ ተማጽነው የመዕላከ እግዚአብሔርን ፀሎት ከምዕመና ጋር ከደገሙ ቡኋላ ቡራኬን ሰጥተው የዕለቱን አስተምህሮዋቸውን አጠናቀዋል።  

 








All the contents on this site are copyrighted ©.