2016-07-28 16:17:00

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮ አብሮአቸው ለተጓዙት ጋዜጠኞች ያስደመጡት ንግግር


ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲ፣ የቅድስት መንበር የዜናና ኅትመት ክፍል ተጠሪ፣ ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ በፖላንድ ክራኩፍ ከተማ በሚከበረው የዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በዓል ላይ ለመገኘት ከአውሮፕላን ጣቢያ ለተነሱት ቅዱስ ኣባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮን በሚሳፈሩበት አየር ተገኝተው አብሮቸው ለሚጓዙት ከ15 አገሮች የተወጣጡ ከ70 በላይ ጋዜጠኞችን ወክለው ሰላምታ አቅርበው መልካም ጉዞን ተመኝተውላቸዋል።  ከቅዱስነታቸው የሚላኩ መልዕክቶች ልኡካን ጋዜጠኞች በስኬት ለመላው ዓለም እንደሚያሰራጩ ተናግረው፣ በጉዞ ላይ እያሉም ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ፍሬያማ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው፣ በዓሉ በሚከበርበት ዋዜማ ላይ፣ በተለይ በፈረንሳይ በአንድ ካህን ላይ ተፈጸመውን ግድያንና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች በሚታዩ ክስተቶች ርእስ ዙሪያ ቅዱስነታቸው የተሰማቸውን እንዲገልጹ አባ ሎምባርዲ ጠይቀዋቸዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አብሮአቸው ለሚጓዙት በሙሉ ምስጋናንና ሰላምታን ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ስለ ዓለም ደኅንነት መጓደል ይነገር እንጂ አሁን እየተከሰተ ላለው አደጋ ትክክለኛው ትርጉም “ጦርነት” ነው ብለዋል። ላለፉት ጊዜያት ዓለማችን ውጊያ ላይ ትገኛለች ስንል ቆይተናል። በአሥራዎቹ፣ በሃያዎቹ፣ በኋላም ከሰላሳዎቹ መጨረሻ እስከ አርባዎቹ አጋማሽ ጦርነቶች ነበሩ። እያንዳንዳቸው በዓይነትም በመጠንም ይለያያሉ። አሁን እየተከሰተ ያለው ጦርነት ግን የተደራጀ ነው ባይባልም የራሱ ስልትና አካሄድ የያዘ ጦርነት እንደሆነ እገነዘባለሁ ብለዋል። ዞሮ ዞሮ ጦርነት ነው። ለመላው ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመጸለይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴን በማሳረግ ላይ እያሉ የተገደሉት ካህን አስታውሰው አያይዘውም ስንት ክርስቲያኖች፣ ስንት ንጹሐን ዜጎች፣ ስንት ሕጻናት እየተገደሉ ይገኛሉ? ለምሳሌ አንድ የአፍሪቃን አገር ናይጀሪያን ብቻ እንውሰድ። ዓለማችን ጦርነት ላይ ነች፣ ሰላምን አጥታለች። ይህን ሐቅ መደበቅ የለብንም ካሉ በኋላ በዓለም አቀፉ የወጣቶች በዓል ወቅት ጋዜጠኞቹ ለሚያቀርቡት አገልግሎቶች ከወዲሁ አመስግነው በዚህ በዓል ላይ ወጣቶች በበኩላቸው ተስፋን የሚሰጥ መልዕክት እንደሚያሰሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በፈረንሳይ ለተፈጸመው ድርጊት መጽናናትን የተመኙትን ቀዱስ አባታችን ሁሉም አመስግነው፣ በስልክ ለተገናኙዋችው የፈረንሳዩን ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ሆላንዴን ከልብ አመስግነዋል። ክቡር አባ ፌደሪኮ ሎምባርዲም በበኩላቸው ቅዱስነታቸውን አመስግነው በእነዚህ ቀናት ውስጥ ጋዜጠኞች ሁሉ ለሰላም አብሮአቸው እንደሚሰሩ አረጋግጠውላቸዋል። ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ በመጨረሻም አሁን እየተደረገ ያለው ጦርነት የሃይማኖት ጦርነት ሳይሆን የጥቅም ጦርነት፣ የገንዘብ ጦርነት፣ የተፈጥሮ ሃብት ለመቆጣጠር ያለመ ጦርነትና፣ አንዱ በሌላው ላይ የበላይነትን ለበጎናጸፍ ታልሞ የሚከወን ጦርነት እንደሆነም አስረድተው ሃይማኖቶች በሙሉ ለሰላም የቆሙ እንጂ ጦርነትን የማካሄድ ፍላጎትም ይሁን ዓላማውም እንደሌላቸው ገልጸዋል።              








All the contents on this site are copyrighted ©.