2016-05-29 14:42:00

ክቡር አባ ጴጥሮስ ካሳኅይ በ96 ዓመታቸው ከእዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።


ክቡር አባ ጴጥሮስ ካኅሳይ ሕይወት ታሪክ

"ሩጫዬን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፣ ሃይማኖቴን ጠብቄያለሁ ከእንግዲህ ወዲህ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል(2ጢሞ. 4፡7)

ክቡር አባ ጴጥሮስ ካህሳይ መጋቢት 14 ቀን 1912 ዓ/ም ከአባታቸው ከአለቃ ካህሳይ ወልደአብና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጸሐይቱ ታደለ እንዳባ ጫሕማ ፂኢ ዝባን ቅስጢ ትግራይ ተወለዱ። ወላጆቻቸው በሁሉም ዘንድ የተመሰከረላቸው መንፈሳውያ ና በእምነታቸው ጠንካሮች ነበሩ። ነገር ግን በአከባቢያቸው በካቶሊክ እምነታቸው ምክንያት ሰዎች ብዙ መከራ አድርሰውባቸዋል፡፡ ለስደትም ዳርጎአቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  “ስለኔ ብሎ ቤቱን፣ ርስቱን፣ ወንድሞቹን፣ ዘመዶቹን የተወ የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል" ያለውን ቃል በማስታወስ አባ ጴጥሮስ የ8 ዓመት ልጅ ሆነው ከመላ ቤተሰቦቻቸው ለሃይማኖታቸው ሲሉ አከባቢያቸውን፣ ርስታቸውንና ዘመዶቻቸውን በመተው ወደ ኤርትራ ተሰደው የካቶሊክ እምነት በሚገኝበት በሰራየ አውራጃ ዐይላ ጉንደት ተብሎ በሚጠራው አከባቢ መኖር ጀመሩ።  

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወላጆቻቸው ከልጆቻቸው አንዱ ካህን እንዲሆንላቸው ትልቅ ምኞት ስለነበራቸው እና ክቡር አባ ጴጥሮስ ድግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ በጸሎተኛ ቤተሰብ ውስጥ በማደጋቸው፡- ካህን የመሆን ብርቱ ጉጉት አድሮባቸው ስለነበር በከረን ዘርአ ክህነት በ1929 ዓ.ም. ገብተው አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ወደ ዓቢይ ዘርዓ-ክህነት በመዝለቅ የ2 ዓመት ፍልስፍናና የ4 ዓመት ነገረ መለኮት (Theology) በንቃት እና በትጋት ተከታትለው ካጠናቀቁ ቡኋላ ግንቦት 25 ቀን 1941 ዓ.ም. በአቡነ ኪዳነማርያም ካሳ እጅ በዓዲ ዜኑ መዕረገ ክህነት ተቀበሉ።

ከክህነት በኋላ በተለያዩ አከባቢዎችና አብያተክርስቲያናት አገልግለዋል፡፡

በ1942 ዓ.ም. ከከረን ከተማ ውጪ 3 ቁምስናዎችን እየተመላለሱ ለአንድ ዓመት ያህል አገልግለዋል፡፡

በ1943 ዓ. ም. ወደ ተራእምኒ ቁምስና ተመደቡ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1944 ዓ. ም. ወደ ሐላይ ተዛወሩ፡፡ በሐላይ ቁምስና 11 ዓመት ከ8 ወር በአገለገሉበት ጊዜ ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ከዋናው መንገድ ወደ ሐላይ የሚያስገባ የመኪና መንገድ በራሳቸው ጥረት አሰርተዋል፡፡ ለአምልኮ አመቺ ያልነበረውን ቤተክርስቲያን ሕዝብን በማስተባበር ራሳቸውም አብረው እየሰሩ የሐላይን ቤተክርስቲያን አሰሩ፡፡ እንደዚሁም የተሟላ የቁምስና ቤት አሰሩ፡፡ የሐላይን ቁምስና በጣም ይወዱ ስለነበር ሕይወታቸው በሙሉ በዚያ ቁምስና መኖር ምኞታቸውና ፍላጎታቸው ነበር፡፡ ሆኖም የሐላይ አከባቢ አየር ለጤንነታቸው ተስማሚ ስላልነበረ 11 ዓመት ከ8 ወር ከአገለገሉ በኋላ ግንቦት 18 ቀን 1955 ዓ.ም. ወደ ሐልሐል ቁምስና ተዛወሩ፡፡ እዚያም ፈራርሶ የነበረውን ቤተክርስቲያንና የቆሞስ ቤት ከራሳቸው ጥሪት ሸጠውና ከበጎ አድራጊዎች ባገኙት ገንዘብ አሟልተው ፈፀሙ፡፡ 5 ዓመት በዚያ ቀምስና ካገለገሉ በኋላ በአለቆቻቸው ፈቃድ ታሕሳስ 18 ቀን 1960 ዓ. ም. ወደ ጎንደር ተዛወሩ፡፡ በጎንደር የኮምቦኒ ማኅበር አባላትን እያገዙ በቁምስና ሥራ አገለገሉ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በሆለታ የዘርአ ክህነት ት/ቤት ተመድበው የዘርዓ-ክህነት ተማሪዎች የነፍስ አባት በመሆንና የግዕዝ ሰዋስው አስተማሪ ሆነው አገለገሉ፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ካተሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስና ቆሞስ ሆነው ተመደቡ፡፡  

ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የቆሞስ መኖርያ ቤት ስላልነበረው፡- ከቤተክርስቲያኑ ጀርባ ወደላይ ከፍ ብሎ ባለው ክፍል ከደወል ቤት አጠገብ 7 ዓመት በስቃይና በተጋድሎ ብርዱን ተቋቁመው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ከበጎ አድራጊዎች እርዳታ ጠይቀው በእነርሱ ቸርነት በተገኘው ገንዘብ በብፁዕ አቡነ አሥራተማርያም ፈቃድ ውብ የሆነ የቆሞስ ቤትና ለቢሮ የሚያገለግሉ ክፍሎች አሠሩ፡፡

በቅ/ገብርኤል ቤተክርስቲያን ለ12 ዓመት ከ4 ወር በታላቅ መንፈሳዊነትና ትጋት ቆሞስ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በ1974 ዓ. ም. ወደ ንኡስ ዘርዓክህነት ተዛውረው ለአንድ ዓመት የዘርዓክህነት ተማሪዎች የነፍስ አባት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ቀጥለውም በአለቆች ፈቃድ ላዛሪስቶችን ለማገዝ ወደ ጅማ ተዛወሩ፡፡ በጅማም በሚያስደንቅ ትጋት ቤተክርስቲያናቸውን አገለገሉ፡፡ሕዝብ ሁሉ ወደዳቸው፡፡ በየቦታው ተበታትነው የነበሩትን ሕዝበ-ክርስቲያን እየመከሩና እያስተማሩ ወደ ቤተክርስቲያናቸው መለስዋቸው፡፡ እዚያው አንድ ዓመት ከ 5 ወር ካገለገሉ በኋላ በሕመም ምክንያት ወደ አዲስአበባ ተልሰው ወደ ኢጣሊያ ለዕረፍት 5 ወር በአለቆች ፈቃድ በተላኩ ጊዜ ጀርመንን፣ ሆላንድን፣ ፈረንሳይንና ኢየሩሳሌምን የመጎብኘት ዕድል አግኝተዋል፡፡ በመቀጠልም በፍሎረንስ ከተማ ኦርዮን ተብሎ ከሚጠራው ማኅበር ጋር ተጠግተው ለአንድ ዓመት ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በቅዱስ አምብሮስ ቁምስና ረዳት ቆሞስ ሆነው ለ3 ዓመት አገልግለዋል፡፡ በመልካምሥራቸው በሚያገለግሉት ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ክብር ስላገኙ በወቅቱ የፍሎረንስ ሀገረስብከት በነበሩት ካርዲናል መልካምሥራቸውን ተመልክተው ሞንተ ዶሚኒ ቁምስና ራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እምነት ጥለውባቸው ቆሞስ ሆነው እንዲያገለግሉ መደብዋቸው፡፡ ካርዲናሉ ለአባ ጴጥሮስ እገዛ እንዲያደርጉላቸው በማሰብ 8 ደናግልና አንድ ዲያቆን መደቡላቸው፡፡ 10 ዓመት በትጋት ካገለገሉ በኋላ በመልካም ሥራቸው ተደስተው የፊዮረንቲና ቤተክርስቲያን ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡

ከተሰጣቸው ቁምስና ጎን ለጎን ሌሎችን ቁምስናዎች በትጋት እገዛ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ መልካም ሥራቸው ተደስተው የፍሎረንስ ካርዲናል ፍሎረንስ ከተማ ለክቡር አባ ጴጥሮስ ሁለተኛ አገራቸው ናት እያሉ በሕዝብ ፊት ደስታቸውንና ለእርሳቸው ያላቸውን ክብርና አድናቆት ይገልጹላቸው ነበር፡፡

በመጨረሻም ክቡር አባ ጴጥሮስ ካርዲናሉን እኔ አሁን እየደከመኝ ነውና ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ብመለስና ባርፍ ይሻለኛል በማለታቸው የፍሎረንስ አቡን ባርከውና መርቀው ገፀበረከት ሰጥተው በትልቅ ክብር ሸኝተዋቸዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአዲስአበባ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ የነበሩትን የመልካም እረኛ ደናግል ማኅበር በቅዳሴ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግለዋል፡፡ በተለያዩ ቁምስናዎች በተለይ በመድኃኔዓለምና በቅ/ሚካኤል ቁምስናዎች በበዓላትና በተጠሩበት በማንኛውም ጊዜ በትጋትና በከፍተኛ መንፈሳዊነት በቅዳሴና ምእመናንን ንስሐ በማስገባት አገልግለዋል፡፡

ክቡር አባ ጴጥሮስ ለእምነታቸው ቀናኢ ለቤተክርስቲያንና ለገቡት የክህነት ቃልኪዳን ፍፁም ታማኝ በመሆን ሕይወታቸው በታዛዥነት አሳልፈዋል፡፡ ክቡር የሆነውን የክህነት ምስጢር እስከመጨረሻው አክብረውት እንዲከበር አድርገዋል፡፡ ክቡር አባ ጴጥሮስ ላመኑበት ዓላማ ወደኋላ የማይሉ መንፈሰ ጠንካራ አባት ነበሩ፡፡ ክቡር አባ ጴጥሮስ በባሕሪያቸው ንቁ፣ ታታሪ፣ ቅንና ከፍተኛ የራስ መተማመን የነበራቸው ትልቁም ትንሹም ከፍተኛ አድናቆት የሚችራቸው አባት ነበሩ፡፡

ክቡር አባ ጴጥሮስ በሕመም ምክንያት የሕክምና ኣርዳት ሲደረግላቸው ከቆየ ቡኋል በግንቦት 12/2008 በ96 ዓመታቸው ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ስርዓት ቀብራቸውም በግንቦት 14/2008 በአዲስ አበባ በቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በክብር አርፉዋል።

ክቡር አባ ጴጥሮስ በሕክምና አገልግሎት እስከመጨረሻው ደረጃ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የረዷቸው ሐኪሞችን ለተደረገልን አገልግሎት ቤተክርስቲያን እያመሰገነች እግዚአብሔር ሥራችሁን ሁሉ ይባርክ እንላለን፡፡

እስከመጨረሻው ደረጃ እስከ ኀልፈተ ሕይወታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አቅማቸው በፈቀደ በሕመማቸው ወቅት ካጠገባቸው ሳይለዩ ላደረጉት እንክብካቤና በሁሉም መስክ ላገለገሉአቸው እህታቸው ወ/ሮ ኤልሳቤጥና ውድ ለጆቻቸው ጽጌረዳ፣ አብረኸት እና ሌሎችም የቤተሰብ አባላት … ቤተክርስቲያን ልዩ ምስጋና ታቀርባለች እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡ቸሩ ፈጣሪ እግዚአብሔር ውለታችሁን ይክፈላችሁ፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት፣ የማህበር ካህናት፣ ወንድሞችና ደናግል፣ ምመናን በሁለንተናዊ እገዛ አባ ጴጥሮስን የረዳችሁት ሁሉ እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡  

እግዚአብሔር ወደራሱ የጠራቸውን አባታችንን ክቡር አባ ጴጥሮስን በመንግስቱ ክብር ያኑርልን፡፡ የሚወዷትና የሚያከብሯት እመ አምላክ ኪዳነምሕረት ነፍሳቸውን ትቀበልልን፡፡ ለሚወዷት ቤተክርስቲያንና ቤተሰባቸው፣ለወዳጆቻቸው ሁሉ እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጠን፡፡

             ቤተ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

             አዲስ አበባ

             ግንቦት 14/2008 ዓ. ም.

 








All the contents on this site are copyrighted ©.