2016-04-27 20:03:00

የር.ሊ.ጳ ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ


ቅ.ኣ.ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ዛሬ ሮብ ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ የተለመደውን ሳምንታዊ የዕለተ ሮብ አጠቃላይ ትምህርተ ክርስቶስ ከማቅረባቸው በፊት ከሉቃስ ወንጌል ‘እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። 

እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው።  እርሱም መልሶ። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ኢየሱስም። እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው።  እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን። ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው።  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥  ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም።  በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም። ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም። ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።’ የሚለው በኤውሮጳ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከተነበበ በኋላ የሚከተለውን ትምህርት ኣቅርበዋል፣

ውድ ወንድሞችና እህቶች! እንደምን ኣደራችሁ! ዛሬ ስለ መልካሙ ሳምራዊ የሚናገረው ምሳሌ እንመለከታለን፣ ኣንድ የህግ መምህር  ኢየሱስን ለመፈተን ‘መምህር ሆይ! ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል’ ሲል ይጠይቀዋል፣ እላይ እንደተጠቀሰውም ጌታ ኢየሱስ ሊቁ መልሱ እንዲሰጥ ይጠይቀዋል ኣያይዞም ያ ጓደኛህን እንደገዛ ራስህ ውደድ በሚለው ነጥብ በማትኮር ‘ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ’ ይለዋል፣ ሰውየው ግን ግራ የተጋባ በመምሰል ጓደኛየስ ማን ይሆን! ቤተሰቤ የኣገሬ ሰዎች ወገኖቼ! አንድ አይነት የእምነት ተከታዮች ባልደረባዎች በማለት የህግ ሊቅ መሆኑን ለማስመስከርና ሰዎችን ጓደኞችና ጎረቤቶችን  የሆኑና ያልሆኑትን ለመከፋፈል ይጠይቃል፡  ጌታ ኢየሱስም የመልካሙ ሳምራዊ ምሳሌ በመጥቀስ ያስረደዋል፣ በምሳሌው ኣንድ ካህን ኣንድ ሌዋዊና ኣንድ ሳምራዊ ሲጠቀሱ ካህኑና ሌዋዊው የእግዚኣብሔር ሰዎች ሆነው ሁሉ ለበጎ ኣድራጎትና ርህራሄ የሚጠባበቃቸው ሲሆኑ ሶስተኛው ግን እንደ ባዳ ኣረሜንና ንጹሕ ያልሆነ ተብሎ በዕብራውያኑ የተገለለ ነበር፣ በኢየሩሳሌምና ኢያሪኮ መንገድ ስለተገኘው በሽፍቶች የተደበደበ ሰው በጌታ ህግ መሰረት ቅድምያ መሰጠትና እርዳታ እንዲለገስለት ሲጠይቅ ካህኑና ሌዋዊው ኣይተው እንዳላዩ ያልፋሉ፣ ምናልባት ካህኑ ቅዳሴ ኖሮት እንዳይዘገይ ሌዋዊውም ደም ኣይቶ እንዳይረክስ የፈራ ሊሆን ይችላል፣ ያም ሆነ ይህ ምንም እርዳታ ሳያደርጉ ያልፋሉ፣ እንድያው መንገዳቸውን የቀየሩም ይመስላል፣  እዚህ ላይ ምሳሌው የሚያስተምረን በእግዚብሔር ቤት የሚመላለስ ሁሉ የእግዚብሔርን ፍቅርና ርህራሄን የተላበሱና የተረዱ አለመሆናቸውና ሌላውን በችግር ላይ የሚገኘውን ለመርዳት ዝግጁ አለመሆናቸውን እንመለከታለን። አንድ ሰው መጽሀፍ ቅዱስን በደንብ አጠናቆ ቢያውቅም የተለያዩ የቴኦሎጂ  ስነ ጽሁፎችን  አጠናቅቆ ቢያውቅም ሁሉንም ያፈቅራል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፍቅርን ለማወቅና   እንደ እግዚብሔር ቃል ለማፍቀር ከእውቀት ባሻገር ሌላው የፍቅር መንገድ የተለየ ነውና።   ከላይ እንደተመለከትነው ካህኑና ሌዋዊው አይተው እንደመርዳት ፋንታ እንዳላዩ ይሆናሉ። ወንድሞቻችንን ከመርዳትና ከማገልገል ፋንታ እንዳላየን ከሆንን እምነታችን ከንቱ ነው። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሰለባ እየተሰቃዩ መሆናቸውንና እንዲሁም በተለያዩ ጦርነቶች አመጻዎች ኢ-ፍትሐዊነት የሚሰቃዩ ሰዎችን ስቃይ እንደ ተመልካች ሆኖ መመልከቱ ተገቢ አይደለም። የሰው ልጅ ስቃይን እንዳላየ ማለፉ ትርጉሙ እግዚብሔርን አለመመልከትና አለማወቅ ነው። እኛ በስቃይ ላይ የሚገኙትን ወንድሞችና እህቶች አዛውንትና ሕጻናት ካልቀረብን ወደ እግዚብ|ሔር መቅረብም አንችልም።

እስቲ ወደ ምሳሌያችን አንኳር እንመለስ። የሰማሪያው ሰው በሁሉም የተናቀው የተደበደበውን ሰው አይቶ በመራራቱ ይረዳዋል እንጂ እንደ ሁለቱ ሰዎች  በእግዚብሔር ቤተ መቅደስ የሚመላለሱት እንዳላየ ሆኖ አልሄደም። አልተወውም የሱ ልብ ራራለት የነሱ ልብ ግን አልተነካም። የሰማሪያው ሰው ልብ ከእግዚብሔር ልብ ጋር የተያያዘ የተተሳሰረ ነበር የነሱ ግን የተዘጋ ነበር። ክርስቶስ ለኛ የሚራራና የሚቆረቆር ነው። ይህንንም ስል በሚደርስብን መከራና ችግር ሁሉ አብሮን ከኛ ጋር እንደሚሳተፍ ነው። በሳምራዊው ሰው ምሳሌነት የክርስቶስን ፍቅርና ርህራሄን እንመለከታለን። ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሲል መወለዱንም እናውቃለን። በዚህም ፍቅር ነው ክርስቶስ በየዕለቱ በሚገጥሙን የተለያዩ የሕይወት ፈተና ገጠሞች ጋር አብሮን ለማጽናናት ዝግጁ ነው። እያንዳንዳችን ይህንን ጥያቄ በልባችን እስቲ እንጠይቅ ? መልሱም ምንም ሐጢአተኛ ብሆንም እንዲሁም ብዙ ችግሮች ቢሆሩኝም  ክርስቶስ ለኔ እንደሚራራ አምናለሁ በማለት በልባችን እናስቀምጠው ። ክርስቶስ እንዲህ ስንለው በፍቅሩ ይነካናል ያቅፈናል ያድነናል። ኢየሱስን ሳይፈልገው ስንቀር በትዕግስት ይጠብቀናል ምንም ግዜም አብሮን ከጎናችን ይገኛል  ።

የሰማሪያው ሰው በእውነተኛ ፍቅርና ርህራሄ ሰውየውን ይረዳዋል ይንከባከበዋል ገንዘቡንም ከፍሎ በጥንቃቄ አስታምምልኝ ተጨማሪ ወጪ ብታደርግም በምመለስበት ግዜ እከፍልሃለሁ ይላል። ይህ ሁሉ የሚያስተምረን ፍቅርን ነው። ፍቅር ዝም ብሎ በቀላሉ የሚወረወር አስተዋጾ ሳይሆን  እንክብካቤና ርህራሄን ይጠቅቃል። ለዚህም ነው የእግዚብሔር ቃል ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ ብሎ የሚያዘን።

በምሳሌው መጨረሻ ላይ ኢየሱስ የሕግ መምህሩን ታዲያ ከእነዚህ ሰዎች በወንበዴዎቹ ተደብድቦ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነለት የትኛው ይመስልሃል ብሎ ሲጠይቀው የሕግ መምህሩም ያ የራራለትና የረዳው ነዋ ሲል መለሰ መልሱም ትክክል ነበር። በመጀመሪያው ምሳሌ ካህኑና ሌዋዊው እንዳላዩ ቢሄዱም ሰማሪያኑ ይጠጋና ይረዳዋል ኢየሱስም የሰውየውን ሃሳብና አመለካከት በመቀየር በመምረጥ መርዳት ሳይሆን ማንኛውንም ሰው እንደራሳችን አድርገን በመውደድ መርዳት እንዳለብን ያስተምረናል ። ለሌላው መራራት።  ይህ ምሳሌ ለሁላችንም ትልቅ ስጦታና ትምህርት ነው ለእያንዳንዳችን ጌታችን ኢየሱስ እንደ የህግ መምህሩ ለሁሉም እንድንራራና እንድንረዳ አደራ ይለናል። ሁላችንም የተጠራነው እንደ የሳምራዊው ሰው የሕይወት ጎዳና እንድንመላለስ ነው የሳምራዊው ሰው ምሳሌ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ክርስቶስ እኛን እንዳፈቀረ እኛም እርስ በእርሳችን መፈቃቀር አለብን ሲሉ የእለቱን ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.