2016-04-19 11:36:00

በቤተ ክርስቲያን ስርዓት እና አስተምሮ መሰረት የፆማችን ስድስተኛው ሳምንት ሰነበተ ኒቆዲሞስ ተብሎ የምጠራል።


የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን ሰነበታችሁ!

ቸሩ እግዚአብሔር አምላካችን ይህንን ወቅት ከእርሱ ጋር የለንን ቅርበት እና ወዳጅነትን ለማጠናከር እንድንጠቀምበት በማሰብ ይህንን የፆም ጊዜ ስል ሰጠን ቅዱስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

በቤተ ክርስቲያን ስርዓት እና አስተምሮ መሰረት የፆማችን ስድስተኛው ሳምንት (ሚያዝያ 9,2018) ሰነበተ ኒቆዲሞስ ተብሎ የምጠራ ሲሆን በዪሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 3: 1-13 በተጠቀሰው መሰረት አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል የፈሪሳዊያን መሪ ወይም ገዢ በማታ ኢየሱስን ለመፈለግ መሄዱን ይገልጻል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ኒቆዲሞስ የፈሪሳዊያን ገዢ ከሆነ ለምን ኢየሱስን ለመፈለግ ሄደ? ለምንስ በማታ ወደ ኢየሱስ መሄድን ፈለገ?  ለምን በቀን አልሄድም ነበር? ኒቆዲሞስ ኢየሱስን ስል ምንድነው ማነጋገር የፈለገው? በወንጌሉ የተጠቀሰው “እንደ ገና መወለድ” ምን ማለት ነው? በአጠቃላይ ይህ የወንጌል ክፍል ለእኛ ምን ያስተምረናል? የምሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል።

ከታሪኩ እንደ ምንረዳው ኒቆዲሞስ ሀብታም የፈሪሳዊ ገዢ ነበረ። ስለዚህ ከሌሎች ፈሪሳዊያን የተሻለ የሚባል ኑሮ መኖር የምችል ሰው ነበር። ታዲያ ለምን ይሁን ወደ ኢየሱስ የሄደው? እንደ ምታወቀው ፈሪስዊያን የህግ ሰዎች ናቸው። ለህግ ትልቅ ቦታ ነው የሚሰጡት፣ ምክንያቱም ህግን ያጎደለ በከፍተኛ ደረጃ ቅጣት ይጠብቀው ነበር። ኒቆዲሞስ ይህንን ሳይውቅ ቀርቶ አይደለም ነገር ግን ምን አልባት ውስጡን ሰላም የነሳው ነገር ሊኖር ይችላል ወይም ሕሊናውን የሚረብሽ ነገር ነበረ ማለት ነው። ይህንን የጎደለውን ነገር ለመጠየቅ ወደ ኢየሱስ  በማታ ሄደ።

ማታ ወይ በጨለማ ወደ ኢየሱስ ለምን ሄደ የሚለው ሁለት ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል።

በመጀመሪያ እርሱ የፈሪሳዊያን ገዢ ስለነበረ ወደ ኢየሱስ ሲሄድ ሌሎቹ ቢያዩት እንዳይ ወቅሱት ስለፈራ ሊሆን ይችላል፣ ምክንያቱም ፈሪሳዊያን ኢየሱስን እንደ መሲህ ስለማይቆጥሩት።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በቀን ኢየሱስ በብዙ ሰዎች ይከበብ ስለ ነበር በነፃነት ልያናግረው ምቹ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል። ስለ እዚህም ኢየሱስ ቢቻውን የምሆንበት ወቀት ማታ  በመሆኑ በነፃነት ብቻውን የልቡን ልያዋየው ፈልጎ ይሆናል የምሽት ጊዜን የመረጠው።

ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ የሄደው ስለ ሀገር ጉዳይ ሊያወያየው ፈልጎ አልነበረም። ስለ ነብሱ እና ስለ ድህንነቱ ጉዳይ ሊያወያየው ፈልጎ እና የደህንነትን መንገድ እንድያሳየው ፈልጎ ስለነበር ኢየሱስ ይህንን መንገድ ይጠቁመው ዘንድ ለመጠየቅ አስቦ ስለነበር ነው።

ለዚህም ነው የነበረውን የጨለማ ኑሮ ትቶ ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ መሄድን የፈለገው። ከዚያም ኢየሱስ እንደገና ተወለድ ብሎት አዲስ ሰው እንዲሆን አደረገው በኢየሱስም አመነ። ነገር ግን በመጀመሪያ ኒቆዲሞኣስ ከኢየሱስ ጋር በምነጋገርበት ወቅት “እንደ ገና መወለድ አለብህ” ስላለው ይህ አባባል ምን ማለት እንደሆነ አልገባው ነበር።

“እንደ ገና መወልድ” ምን ማለት ነው? ሁላችንም አንድ ጊዜ በስጋ ተወልደናል። ነገር ግን ኢየሱስ ኒቆዲሞስን “እንደ ገና መወለድ” አለብህ እንዳለው ሁሉ እኛም እንደ ገና በመንፈስ መወለድ ይጠበቅብናል የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ። ክርስቲያኖች ሁላችን በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል የልጅነት መንፈሱንም ተቀብለናል። ይህ የተቀበልነው የክርስትና መንፈስ ሁል ጊዜ መታደስ ይኖርበታል፣ በእግዚአብሔር መንፈስ እና ሐሳብ ሁል ጊዜ መኖር የጠበቅብናል፣ በንጸህና መኖር እና የእግዚአብሔርን ፀጋ እንደ ልብስ መልበስ ይጠበቅብናል። በተለይም በዝህ የፆማችን ወቅት መሳሌያዊ የሆነ ኑሮን በመኖር፣ መንፈሳዊ ተግድሎን በማድረግ፣ እንዲሁም የተቸገሩትን ወንድም እና እህቶቻችንን በመርዳት እና ካለን በማካፈል የእግዚአብሔር ልጅ መሆናችንን በተግባር ላናስመሰክር ገባናል።

በወንጌል ውስጥ ብዙን ጊዜ እንደ “ገና ካልተወለዳችሁ” የሚሉት ቃላት የምያስረዱን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት የእግዚአብሔርን የልጅነት መንፈስን ለማግኘት፣ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ “እንደ ገና መወለድ” ያስፈልጋል። ልባችንን መንጻት ይኖርብናል።

ዛሬ ስነበብ የሰማነው የወንጌል ቃል ለእኛ ምን ያስተምረናል?

ሀብታሙ የሀገር ገዢ የሆነው ኒቆዲሞስ ኢየሱስን ፍለጋ ሄደ። አንድ አንድ ጊዜ ገንዘብ፣ ሀብት፣ ስልጣን ሰላምን ይሰጡናል በለን እናስብ ይሆናል። ፈጹም እና የማይነጥፍ ሰላም የሚሰጠን እግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ብቻ ነው የሕሊና ሰላም እና እረፍትን ሊሰጠን የምችለው። ለዝህም ነው ሕሊናችን ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ለማነጋገር የሚጓጓው። በጽሞና ልብ ብለን እግዚአብሔርን መፈለግ የጠበቅብናል የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ።

ኒቆዲሞስ የነበረው ሀላፊነት እና ሁኔታ ምንም እንኳን ኢየሱስን ለማግኘት ምቹ ባይሆንለትም እንደ ምንም ብሎ ተደብቆም ቢሆን በማታ ሄዶ ኢየሱስን አገኘው። በጨለማ ሄዶ ብርሃንን ለብሶ ተመለሰ። አዲስ ሊባል የምችል የሕይወት አቅጣጫ ይዞ ተመለሰ።   

እኛም አንድ አንድ ጊዜ የምንኖርበት ሁኔታ፣ ባህል፣ አከባቢ የመሳሰሉ ነግሮች ኢየሱስን እንድነገናኝ ምቹ ሁኔታዎችን ልፈጥሩ አይችሉ ይሆናል። የሕይወት ፈተናዎች እና ወጣ ወረዶች ልበዙም ይችላሉ። ነገር ግን እኛም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ በማጤን ወደ ኢየሱስ በሙሉ ልባችን ተመልሰን ማንነታችን ወደ እራሱ ማንነት እንዲ ቀይር እና እውነተኛ ደስታን ይሰጠን ዘንድ መንገድ ያሳየን ዘንድ ወደ እርሱ መመለስ ይጠበቅብናል።

ዛሬ ብዙ ኒቆዲሞሶች ልንኖር እንችላለን፣ ወደ ኢየሱስ ደፈረን መሄድ ያቃተን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የምያስፈራን፣ ንስሐ መግባት የምያስፈራን፣ ሐጥያታችንን መናዘዝ የምያስፈራን። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ ከኒቆዲማስ ሕይወት እንደ ተማርነው እኛም ያለመንም ፍርሀት ኢየሱስን ለመገናኘት መስዋዕትነትን መከፈል የጠበቅብናል በተለይም በዝህ የጾም ወቅታችን። ምክንያቱም አንድ እና አንድ ብቻ ነው. . . አዲስ ሕይወት ይሰጠናል ኑሮኋችንን በድስታ ይሞላልናል።

ኒቆዲማስ በጨለማ ወደ ኢየሱስ ሄደ። ኢየሱስ ግን ጨለማን ቀይሮ በርሃንን አጎናጸፈው የዘላለም ሕይወትም ሰጠው። “እንደ ገና መወለድ” የሂደት ጉዳይ መሆኑን ተርድተን ቀስ በቀስ ከዝህ የጨለማ ሕይወት በመላቀቅ ኢየሱስን ሁል ጊዜ መፈለግ ይጠበቅብናል፣ የሕይወታችን እና የደስታችን ምንጭ እርሱ ብቻ ስለሆነ።

እግዚአብሔር እንደ ገና በመንፈስ የምንወለድበትን ፀጋ ለሁላችንም አብዝቶ ይስጠን።

አሜን።

 








All the contents on this site are copyrighted ©.