2016-02-03 16:31:00

ብፁዕ ካርዲናል ቦ፦ ጦርነትንና አሳር ለማሸነፍ የጋራ ውይይትና አንድነት ማጽናት


እ.ኤ.አ.  ከጥር 25 ቀን እስከ ጥር 31 ቀን 2016 ዓ.ም. በፍሊፒንስ ሰቡ ሰበካ “የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው” በሚል ከሓዋሪያው ጳውሎስ  ወደ ቆላስይስ ከጻፈው መልእክት ምዕ. 1 ቁጥር 27 በተወሰደ ቃል ሥር ተመርቶ የተካሄደው 51ኛው የአለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉብኤ መጠናቀቁ ቀደም ተብሎ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮን በጉባኤው እንዲወክሉዋቸው የሰየሙዋቸው ከቅዱስ አባታችን የተላለፈው መልእክት በማስደመጥ ጉባኤውን በንንግር የከፍቱትና በመዝጊያው ቀን ያረገው መሥዋዕተ ቅዳሴ የመሩት የቢርማንያ ርእሰ ከተማ ያንጎን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማኡንግ ቦ ባስደመጡት ስብከት ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ካለ መታከት እንደሚሉት በዓለም የሚታዩት ጦርነቶችና አሳር ሁሉ ለማስወገድ ውይይትና አንድነት መሠረት መሆኑ በስፋት ማብራራታቸው ሲገለጥ፣ ስለ ተካሄደው ጉባኤ በማደገፍ ብፁዕነታቸው ከቫቲካን ረዲዮ ጋር በስልክ ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፦ በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል የሚጸናው የጋራው ውይይትና የሁሉም ኃይማኖቶች መጣጣም ለዓለም ሰላምና መረጋጋት እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በየዕለቱ የሚገልጡት ሃሳብና የሚኖሩት ተግባርም ነው። በተለያዩ ኃይማኖቶች መካከል ያለው ልዩነት ድካምነት ሳይሆን ለመቀራረብ የሚያነቃቃ እምቅ ኃይል ነው፣ ስለዚህ ልዩነቱ በአንድነት መንፈስ ከተኖረ በዓለም በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱት ልዩነቶች ሁሉ እንደ ሃብት ታይተው ለመተዋወቅና ለመቀራረብ ምክንያት ይሆናሉ፣ ስለዚህ ልዩነት ብርታት እንጂ ድካምነት አይደለ ብለዋል።

በዓለም የሚታየው እርሃብና ድኽነት ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ብለው ለምን እንደገለጡት ሲያብራሩ፦ እርሃብና ድኽነት እንዲቀረፍ ሁሉም አገሮችና መንግሥታት በጋራ መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚገባችው የሚጠራ ሃሳብ ነው። ችግሩ ሊቀረፍ ይችላል፣ የሚቀረፈውም የዓለም ሃብት በእኩል ሲዳረስ ነው። መፍትሔው ይኽ መሆኑም ሁሉ ያውቀዋል። በዓለም የተፈጥሮ ሃብት ባለ መኖሩ ሳይሆን የዓለም ሃብት በጥቂቱ  እጅ ቁጥጥር ውስጥ በመሆኑ ነው። እርሃብ ያለው እኮ በዓለም የምግብ እጥረት ስላለ ሳይሆን ሰው ማእከል ያለ ማድረግ ባህል እያመጣው ያለው ስግብግብነት ነው። ምግብ መጠለያ እና ሕንጸት የአገልግሎት መስጫ ሁሉ ለስው ልጅ መሠረታውያን አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው ስለዚህ ይኸንን መሠረታዊው ፍላጎት ማርካት ግዴታ ነው። አለ ምግብ አለ መጠለያ አለ ሕንጸት አለ የሕክምና አገልግሎት የሚኖር ሰው ለዓለም የሕሊና ጥያቄ ነው። ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ በሁሉም የዓለም ሕዝብ የሚወደዱና የሚደነቁ መሆናቸው አያጠያይቅም፣ ብዙ መሪዎችም ቅዱስነታቸውን የሰብአዊ አብነት በማለት ይገልጧችዋል፣ እንዲህ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸውም ሰብአውነት ማእከል የማድረግ ባህል ለማስፋፋት የሚያደርጉት ጥረት ነው። ለእኛ ካቶሊኮች የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ በመሆናቸውም ጭምር ነው። እሳቸው የሚሰጡት ትምህርትና ቃል በእውነቱ ወንጌላዊ ቤተ ክርስቲያናዊ ቃል ነው፣ በመሆኑም ይኸንን ቃል አዳምጦ እግብር ላይ ማዋል እርሃብ ጦርነት የመሳሰሉት ሰው ልጅ ለተለያየ አደጋ የሚያጋልጡት እንከነኖች ሁሉ ለመቅረች ይቻላል በማለት ያካሄዱት ቃለ ምልልስ እዚህ ላይ አጠቃለዋል።

ይኽ በእንዲህ እንዳለም ብፁዕ ካርዲናል ቦ የጉባኤው መዝጊያ ያረገው መሥዋዕተ ቅዳሴ መርተው ባስደመጡት ስብከት ማንኛውም ዓይነት በቤተሰብ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ከአቶሚካዊና ከሽበራዊ ጥቃት የባሰ ነው። በሕይወት ላይ ቤተሰብ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት የሞት ባህል በሚል ቃል ገልጠው፣ በፊሊፒንስ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሦስተኛው ሺሕ ዘመን የአስፍሆተ ወንጌል የሕይወት ባህል አብነት ነች፣ ቤተሰብ ቀዳሚው የቅዱስ ቁርባን ቦታ ነው። በቤተሰብ ውስጥ የሚዘራው ቅዱስ ቁርባን ያብባል ምክንያቱም እርሷ ዕለት በዕለት እንጀራ የሚቆረስባት ቅዱስ ሥፍራ ነችና። ስለዚህ እንክብካቤ ያስፈልጋታል እንዳሉ ኤሺያን ኔውስ የዜና አገልግልቶ አስታወቀ።

ብፁዕ ካርዲናል ቦ ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ ብፁዓን ካርዲናል ጳጳሳት ካህናት ደናግል ምእመናን በጠቅላላ ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች ቅዱስ ቁርባን በሚል ቅዱስ ቋንቋ ሥር ያሰባሰበው የተካሄደው የዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጰራቅሊጦስ በማለት ገልጠው የኩላዊት ቤተ ክርስቲያን መግለጫም እርሱ ነው ብለው። የፊሊፒንስ ሕዝብ ተጋባእያኑ በመቀበል በማስተናገድ ያሳየው ቅርበትና እንክብካቤ በእውነቱ የፊሊፒንስ ሕዝብ የሐሴት ሐዋርያ መሆኑ ያረጋግጥልናል እንዳሉ ኤሺያን ኔውስ የዜና አገልግሎት አመለከተ።

ፊሊፒንስ ለሦስተኛው ሺሕ ዘመን ተልእኮ አብነት

ብፁዕ ካርዲናል ቦ ባስደመጡት ስብከት ፊሊፒንስ ለሦስተኛው ሺሕ ዘመን ተልእኮ አብነትና ማእከል ሲሉ ገልጠው፣ ፊሊፒንስ በእስያ ክፍለ ዓለም ከሚገኙት አገሮች ውስጥ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ምእመን ብዙሃን የሆኑባት አገር በመሆንዋ ገልጠው፣ ይኽ ጸጋ ለዓለም ብርሃንና ጨው እንድትሆን ያደርጋታል። ፊሊፒንስ ተስፋ ያስፈልጋታል ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ያስፈልጋታል፣ ቤተሰብ ተስፋ ያስፈልገዋል፣ ፊሊፒንስ የዚህ ተስፋ ሐዋርያ ነች፣ ምንም’ኳ ድኽነት የሚታይባባት ዘርፈ ብዙ ተጋርጦ ያለባት አገር ብትሆንም ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እምቅ ኃይል ነች። ፊሊፒንስ በዓለም ያች ቃል ኪዳን ባሰሩት ሰዎች መካከል እምብዛም ፍች የማይታባት፣ ሚስጢረ ተክሊል የሚከበርባት አገር ነች እንዳሉ ኤሺያን ኔውስ የዜና አገልግሎት አስታወቀ።

ቅዱስ ቁርባን ለሕይወት ምንጭና ብሶል ነው

ብፁዕ ካርዲናል ቦ ይልሉ፣ የሕይወት ባህል ምንጭ የሕይወት ባህል ለማስፋፋት ለሚደረገው ትግል ብሶልና ለገዛ እራሱ ለሕይወት ባህል ልዩ አብነት ነው። ስለዚህ የቅዱስ ቁርባን ልኡክ መሆን ማለት በቅዱስ ቁርባን ኃይል ተሞልተህ ቅዱስ ቁርባናዊ ሕይወት መኖር ማለት ነው። ቤተሰብ የመጀመሪያ ቁርባን ልዩ ስፍራ ነች፣ ስለዚህ የመጀመሪያ ቁርባን ስንቀበል የተሰማን ልዩ መንፍሳዊነት ህያው በማድረግ ዘወትር በቅዱስ ቁርባን ፍቅር ተደግፈን ክርስትናችን እንኑር፣ ቅዱስ ቁርባን እውነተኛ ህላዌ ነው። የተልእኮና ያገልግሎት ምንጭና ብሶል ነው በማለት ያስደመጡት ስብከት እንዳጠቃለሉ ኤሺያን ኔውስ የዜና አገልግሎት ገለጠ።








All the contents on this site are copyrighted ©.