2015-11-23 16:43:00

የባንጉይ ካቴድራል አለቃ፦ የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ጉብኝት ጸጋና ተስፋ ነው


ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ እ.ኤ.አ. ከህዳር 25 ቀን እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሦስት የአፍሪቃ አገሮች እርሱም በከኒያ ኡጋንዳና ማእከላዊት ረፓብሊክ አፍሪቃ የሚያካሂዱት ዓለም አቀፋዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት በዚህ በአሁኑ ወቅት ዓለም ውጥረትና አመጽ በተሞላችበት ወቅት ሰላም የሚያነቃቃ መሆኑ በመካከለኛይቱ ረፓብሊክ አፍሪቃ ርእሰ ከተማ ባንጉይ ለሚገኘው ካቴድራል አለቃ አባ ማተው ቦንዶቦ በስልክ ከቫቲካን ርዲዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ገልጠው፣ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ያወጁት የምኅረት ቅዱስ ዓመት በይፋ የሚከፈትበት ቀን በተቃረበበት ወቅት ይኸንን ቅዱስ ዓመት ቀደም በማድረግ በመካከለኛይቱ ረፓብሊክ አፍሪቃ ቅዱስ በር በመክፈት የሚፈጽሙት ሐዋርያው ጉብኝት ለሕዝቡ ምህረትን ለመጸገው የመጣው እግዚአብሔር ትእምርት ነው። ቅዱስ አባታችን ያንን በስቃይ በጦርነትና በመለያየት ምክንያት ለጉዳት ተጋልጦ ላለው ሕዝብ በእምነት ለማጽናትና የሚፈጽሙት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለካቶሊክ ምእመን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አቢይ የተስፋና የሰላም ምልክት ነው ብለዋል።

የአገሪቱ ሕዝብ ዓመታት እያስቆጠረ ካለው ዓመጽ ስቃይና ግጭት ነጻ ወጥቶ ሰላም በማረጋገጥ በተረጋጋ ሕይወት እንዲኖር የሚያነቃቃ ሰላም የሚዘራ ሁሉም የሰላም ገንቢ እንዲሆን የሚጠራ ሐዋርያዊ ጉብኝት ነው። የቅዱስ አባታችን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጌታ ሰላሙን እንዲያወርድ ለሚደረገው ጸሎት መልስ ነው ብለዋል።

የቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ሰላም የሚመራ ሁሉም በሰላም ጎዳና እንዲጓዝ የሚደግፍ ነው። በባንጉይ የሚገኘው ካቴድራል ቅዱስ በር ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ሲከፈት ይኽ በቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ የሚፈጸመው በታሪክ ቀዳሜ ነው። በመሆኑም በእውነቱ የእግዚአብሔር ትእምርት ነው። እግዚአብሔር ለመካከለኛይቱ ረፓብሊክ አፍሪቃ የሰጠው ጸጋ ነው በማለት ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።








All the contents on this site are copyrighted ©.