2015-11-14 16:26:00

የአስተምህሮ የመጀመሪያ ሰንበት 15-11-2015 ዓ.ም. “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን በግልጥ ይከፍልሃል ” (ማቴ. 6፡6)


 

የዛሬው ወንጌል “ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ” ብሎ ይጀምራል፡፡ “ግብዝ” ማለት ያልሆነውን ሆኖ መታየት፣ልክ እንደ ድራማ ተዋናይ ሌላ ገጸ-ባሕሪ ለብሶ መጫወት ወይም ደግሞ የጸሎተኛና የመንፈሳዊ ሰው ጭንብል አድርጎ ዋናውን እሱነቱን ደብቆ የሚመላለስ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው በአጭሩ ያልሆነውን ሆኖ ሚቀርብ እና በከንቱ የሚደክም ነው ጸሎቱም በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የለውም፡፡

ጌታችን ሲያስተምር ግን “አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ” ነው ያለው፡፡ ይህ ክፍል ከሌሎች ክፍሎች የተለየ ነው፡፡ ልዩ እና ውድ ስለሆነም ያልተገባ ሰው አይገባበትም፡፡ የጌታችን መልዕክትም ይህ ነው - ይህ ስፍራ አንድ አማኝ ከጌታው ጋር ብቻ ለብቻ የሚገናኝበት፣ ሌሎች ተጻይ ድምጾች የማይስተናገዱበት ስፍራ ነው፤ የዚህ እልፍኝ በር ተዘገቶ ዓለምና ተራ ጭንቀቶቿ ሁሉ ውጪ እንዲቀሩ ይደረጋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ነው አንድ አማኝ ለብቻው ከአምላኩ ጋር እንዲነጋገር የሚመከረው፣ ለዚህም ጌታችን ራሱ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፤ ቀን ቀን ሐዋርያዊ ተግባሩን ሲያከናውን ይቆይና ሌሊት ብቻውን ወደ ተራራ ሄዶ ወደ አባቱ ይጸልይ ነበር (ማቴ፣14፡23፤ ሉቃ 6፡12)፡፡ ስለዚህ በዛሬው ወንጌል በስውር ጸልይ ሲል በሰው የመታየት ፍላጎትንና ፈተናን ለማምለጥ እንድንችል እና ከእግዚአብሔር ብቻ የሚመጣውን በረከት እንዳናጣ ለማሳሰብ ነው፡፡

ይህን ዓይነት የብቻ ጸሎት ስንለማመድ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ማስተዋል ያስፈልጋል፤

ወደ ማን እንደምንጸልይ ማወቅ፤ በመጽሐፍ “አምላካችን የሚያጠፋ እሳት ነው” የሚል ተጽፎ እናነባለን (ዕብ 12፡28-29)፤ ስለዚህ በፈጣሪ ፊት ማሾፍ ከባድ ነው፤ በሱ ፊት መቀለድም አንችልም ይህ አምላክ የልብሱ ዘርፍ ቤተመቅደሱን የሚሞላና በመላዕክትና በቅዱሳን ተከብቦ የሚኖር ነውና፡፡ (ኢሳ 6፡1-3)
ወደዚህ አምላክ ለመቅረብ የቻልነው የደም ዋጋ ስለተከፈለልን ነው፡፡ “በእርሱ እንደ እግዚአብሔር ባላጠግነት መጠን በደሙ በተደረገ ቤዛነት የኃጢአትን ይቅርታ አገኘን” (ኤፌ 1፡7)፡፡
በጸሎታችን ወቅት ደገሞ ፣በተለይ በድካማችን ጊዜ ልዩ የሆነ የመንፈስ ቅዱሰ እርዳታ እንደሚኖረን ማመን እና መጽናት (ሮሜ 8፡26) እንደመንፈስ ቅዱሰ ምሪትም መጸለይ፡፡
በእኛና በእግዚአበሔር መካከል ግንኙነት እንዳይኖር የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ ማጥፋት፤ ከሁሉ በፊት ደግሞ ኃጢአትን መጸየፍ፡፡ ዳዊት “ኃጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ባልሰማኝ ነበር” ነው ያለውና (መዝ 65(66)፡18)

እንግዲህ እግዚአብሔር የንጹህንና የትሁትን ሰው ጸሎት ይሰማልና እንደ ንጹህ መስዋዕት መልካም መዓዛ ያለውን ጸሎታችንን በስውር ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ በእርሱ ጸጋ እና ብርሃን ለመመላለስ ያብቃን፤ አሜን!

ሠላም ወሰናይ

አባ ዳዊት ወርቁ

ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.