2015-03-28 18:55:00

በዓለ ሆሳዕና


«ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፤በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡» (ማቴ 21፡9)

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል ከማክበራችን በፊት ያለው ሰንበት ሆሳዕና ተብሎ ይጠራል፤ በዚህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳልም የገባበት ቀን ይዘከራል፡፡ ዕለቱን አስመልክቶ ከሚነበብልን የወንጌል ቃል ብዙ ትምህርት እናገናለን፣ በተለይም የመዳናችን ቀን መቅረቡን እንረዳለንና እኛም በበኩላችን ራሳችንን እንድንመረምር፣መንፈሳዊ ዕድገታችን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንድናይና ባጎደልነው ተጸጽተን ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት እናደርግ ዘንድ ተገቢ ነው፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች በሆሳዕና ቀን ዘምረውና ክርስቶስን አሞግሰው፣በስቅለተ ዓርብ ቀን ግን «ይሰቀል» ብለው አብዝተው ይጮሁ ነበር፡፡ የነዚህ ሰዎች እምነት የጸናች አልነበረችምና በዘመኑ በነበሩት የካህናት አለቆች እና መምህራን ሽንገላ ከትክክለኛው መንገዳቸው ወጡ፤ከኢየሱስ ይልቅ በርባንን መረጡ፤በሆሳዕና ቀን «ንጉሣችን» ብለው ዘምረው በስቅለተ-ዓርብ ቀን (ከአምስት ቀናት በኋላ) ደግሞ «ደመኛችን ነው» አሉ፤ ቀድሞ ልብሳቸውን እንዳላነጠፉለትና የተቀመጠባት አህያ እንድተራመድበት እነዳላደረጉ ሁሉ፣በኋላ የሱን ልብስ ዕጣ ተጣጥለው ተከፋፈሉት፤ «ይንገሥ» ባሉበት አንደበት መልሰው «ይሙት»፣«ይሰቀል» ብለው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮሁ፤ ስለ መሲሕ መምጣት ግድ ያልነበረው ጲላጦስ እንኳ እነሆ ንጉሳችሁ ቢላቸው፣እንደውም «ከዚህ ሰው ደም ንጹህ ነኝ» ብሎ በፊታቸው እጁን ቢታጠብም በደሉ በእኛ ብቻ ሳይሆን በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን ብለው በመማማል እንዲሞት አጥብቀው ለመኑ፡፡

እስቲ ራሳችንን በነዚህ ሰዎች ቦታ እናሰቀምጥና በዚህ በዓልና በዓርብ ስቅለት ቀን እዚያ ብንገኝ፣በነሱ መካከል ብንሆን ኖሮ ምን እንል ነበር? ምናልባት በቃላችን «ይሰቀል» ባንልም በዘመናችን ክርስቶስን በተለያየ መንገድ እናሰቃየው፣እንሰቅለው ይሆናል፡፡ የወንጌልና በኢየሱስ የሚያምኑ እውነተኞች ክርስቲያኖች ጠላት ከሆንን ክርስቶስን እያሳደድነውና እየሰቀልነው መሆናችንን አንርሳ፡፡ በኑሮ አለመመቻቸት፣በዕቅድ አለመሳካት፣በእምነታችንና በሃይማኖታችን ስንፈተን ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በጌታ ቀኝ የተሰቀለውን በደለኛ ቃላት በእምነት መድገም ያስፈልጋል፣«አስታውሰኝ» ማለት፡፡ ክርስቶስን በማንኛውም ፈተና ውስጥ ስንገኝ «አስታውሰኝ» የማለቱ እምነትና ልምድ ካለን በእርሱ ዕርዳታ የማናልፈው ፈተና አይኖርም፡፡ ስለዚህ እንደቀደሙት ሐሳባችንን እየቀያየርን ሲመቸን ብቻ ማመን ወይም ደግሞ ሚዛን ወደደፋበት መቀላቀል ሳይሆን ክርስቶስን ይዘን መጽናት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡ ምክንያቱም «ትንሣኤ ያለው ሁሌም ከጎለጎታ በኋላ ነው»፡፡

ሠላም ወሰናይ!

መልካም በዓለ ሆሳዕና ያድርግልን

 

አባ ዳዊት ወርቁ

ዘማኅበረ ካፑቺን








All the contents on this site are copyrighted ©.